‹‹ ይህች ቦታ ለኛም ለነፋሱም ትመቸናለች፡፡ እንጦጦ ብርድ ነዉ፡፡
እዚህ ከተማ እናብጅ፡፡ ቦታዋንም አዲስ አበባ ብያታለሁ፡፡›› እቴጌ ጣይቱ
‹‹ እቴ አዲስ አበባ ብለሽ መሰየምሽ ደግ አድርገሻል፡፡ አዲስ አበባ
በያት፡፡›› ዳገማዊ አጼ ምኒልክ
ጸሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ ስለ አዲስ አበባ አመሰራረት ሲናገሩ ‹‹
… ጣይቱ ከድንኳናቸዉ በር ሆነዉ ሲመለከቱ የአካባቢዉን የተፈጥሮ ዉበትና የአየር ንብረት ሁኔታ በማድነቃቸዉ ምኒልክን ፍል ዉሃ
አካባቢ ቤት ለመሥራት እንዲፈቀድላቸዉ ጠየቁ፡፡ ምኒልክም ፈቃደኛ ሆነዉ የቤቱ ሥራ በፍጥነት ተጀመረ፡፡›› ይለናል፤
የአዲስ አበባ 100ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት የተዘጋጀዉ የበዓሉ
ማክበሪያ መጽሔትም ‹‹ … አዲስ አበባ ከ1883 - 1979 ዓ.ም. ድረስ በርዕሰ ከተማነት የተጫወተችዉ ሚና እጅግ በጣም ብዙና
መሠረታዊም ነዉ፡፡›› በማለት ስለአዲስ አበባ ርዕሰ መዲናነት ያስነብበናል፤ ዛሬም አዲስ አበባ የአፍሪካ አገራት መዲና ሆና እንዳለች
እኛ የዛሬዎቹ ትዉልድ የዓይን ምስክሮች ነን፡፡
በአንድ ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ክቡር መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን
መስኮት ስለ አዲስ አበባ ሲናገሩ ‹‹ … አዲስ አበባ አሁን እንደምታዩዋት ለነዋሪ ምቹ አይደለችም ስለዚህ አሁን ካላት ሶስት መልክ
ቢያንስ ወደ ሁለት ልናጠጋጋት ግድ ይላል፤ ስለዚህ እንደገና እንሰራታለን …›› ብለዉ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ፡፡አጼ
ምኒልክም አዲስ አበባን ሲቆረቁሩዋት ከጫካነት ነበር መነሻዋ አሁንም ከ100 ዓመት በኃላ ከጫካ የማትሻል ጎስቋላ ከተማ ናት ነገር
ግን የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ ለዚህ ነዉ አሁንም አዲስ አበባ እንደገና መሰራት ያስፈለጋት፤ እየተሰራችም ትገኛለች፡፡
አዲስ አበባ ትናንት በአራቱም ከተማ እንጨትና የተለያዩ ቁሳቁሶች የጫኑ
አህዮች ይመላለሱባታል አሁንም እንደዚያዉ!
አዲስ አበባ ስልጣኔ ዳዴ እያለ በግድ የገባባት የነበረች አገር ነበረች
ዛሬም ዳዴ እያለባት ያለች አገር ነች፤(ንፁህ የመጠጥ ዉሃ አልነበራትም ዛሬም የላትም ጠጥቶ ከሚያድረዉ የሚጠማዉ ይበዛል! የኤሌክትሪክ
ሐይል ታገኝ የነበረዉ 24 ሰዓት አልነበረም አሁንም ሲፈልጋቸዉ በፈረቃ ሲፈልጋቸዉ ባፈለጋቸዉ ሰዓት መብራት ሐይሎች መብራት የሚያጠፉባት
አገር ነች አዲስ አበባ! ስልክ የሰይጣን ስራ ነዉ ተብሎባት ስለድንቁርና የሚሰበክባት አዲስ አበባ ዛሬም ጥርት ያለ የስልክ አገልግሎት
ባለመኖሩ በድንቁርና ዉስጥ ትገኛለች! አዲስ አበባ ከ100 ዓመት በኃላ፤ የአዲስ አበባ ቤቶች ከ100 ዓመት በፊት ጣል ጣል ብለዉ
የሚታዩ የሳር ቤቶች ይታዩባት እንደነበር ዛሬም ምንም እንኳን ከመጨናነቋ የተነሳ ንፁህ አየር እንኳን ለማግኘት የምታስጨንቅ ጥቅጥቅ
ያለች መፈናፈኛ የሌላት ብትሆንም አብዛኛዉ የነዋሪዎቿ መኖሪያ ጣሪያ ከሳር ቤት አይሻልም ክረምት በመጣ ቁጥር የሚያፈስ እና ጥገና
የሚያስፈልገዉ በቆርቆሮ ላይ ላስቲክ የሚለብስ ነዉ፤)
‹‹ አዱ ገነት›› ስትባል ሰምቻለሁ ገነት እንደ አዲስ አበባ ከሆነች
ትቅርብኝ፤ … የምታስብል ከተማ ነች!
አዲስ አበባ 100ኛ የልደት በዓሏን ያከበረችዉ በደርግ ዘመነ መንግስት
እንደመሆኑ መጠን የወቅቱ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባል የአዲስ አበባ አጠቃላይ የከተማ ነዋሪዎች ምክር ቤት ሊቀመንበርና
ከንቲባ የሆኑት ጓድ ዘዉዴ ተክሉ ስለ አዲስ አበባ በተናገሩበት ወቅት፡-
·
‹‹
… የእንጦጦ ከተማ መቆርቆር ለአዲስ አበባ ከተማ መመረጥ ዋዜማ እንደነበር ይታወቃል፡፡››
·
‹‹
… የዛሬዋ አዲስ አበባን ዳግማዊ አፄ ምኒልክና ጣይቱ በኅዳር 1879 መቆርቆራቸዉን የተለያዩ የታሪክ ሰዎችን የዕድሜ ባለጸጋ አረጋዉያን
አረጋግጠዋል፡፡በዚህም መሠረት በኅዳር 1979 የአገራችን የኢትዮጵያ መዲና የአዲስ አበባ ከተማ አንድ መቶ አመቷን ታከብራለች፡፡››
·
‹‹
… አዲስ አበባችን በ264 ቀበሌዎች፣ በ25 ከፍተኞችና በአንድ አጠቃላይ ምክር ቤት መዋቅራዊ አደረጃጀት ተከፍላ ዲሞክራሲያዊ በሆነ
መንገድ በነዋሪዋ ሕዝብ ተመራጮች እየተዳደረች ነዉ፡፡
·
‹‹
ከተማችን እንደስሟ ያማረች እንድትሆን ይበልጥ ለመሥራት እንድንነሳ እየጠየኩ ለአዲስ አበባችን 100ኛ ዓመት በዓል አከባበር እንኳን
ደረሳችሁ ለማለት ይህንን ታሪካዊ ዕድል በማግኘቴ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ እገልፃለሁ፡፡›› በማለት ነበር መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ እንጦጦን የቆረቆሩት በዘፈቀደ ነዉ ለማለት ባያስደፍርም
የዘመናቸዉ አስተሳሰብ እና ስልጣኔ በሚፈቅደዉ ከነባራዊዉ ነገር ጋር በማጣጣምና በሚመች ሁኔታ ለኑሮ ተስማሚ ስለመሆኑ ታስቦበት
ሳይሆን የቦታዉ አቀማመጥ ዙሪያ ገባዉን ለመቆጣጠር የሚያስችልና ለዘመኑ የመከላከል ስልት በነበረዉ አመቺነትና የሌሎችንም የወቅቱን
መመዘኛዎች የሚያሟላ በመሆኑ እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን፡፡ ምንም ይሁን ምንም በሰዓታቸዉ ማድረግ ያለባቸዉን አድርገዉ አልፈዋል፤
እኛ የቆምነዉ እነሱ በጣሉት ጠንካራ መሰረት ላይ ነዉና በመልካም እንዘክራቸዋለን፡፡
የእንጦጦ ከተማ ብርዳማና ለጤና የማይስማማ መሆኑ ሲታወቅና የዛሬይቱ
አዲስ አበባ የትላንትናዋ ፊንፊኔ ብዙ ሳይቆይ ሌሎች መስፈርቶች ተጨምሮ ለኑሮም ተስማሚነቷ ታዉቆ በእይታቸዉ ልትገባና ለከተማነት
ልትቆረቆር በቅታለች፤ ረባዳማዋ ፊንፊኔ በተለያዩ መመዘኛ ተመዝና አልፋ የነገስታቱ መቀመጫ ሆነች ዛሬ እኛም እንራኮትባታለን የመጡ
ሁላ ይሰለጥኑባታል ጥቂቶችም ባለሥልጣን ይሆኑባታል የታደሉት ደግሞ እንደገና ሊሰሯት መዋዕለ ነዋያቸዉን ያፈሱባታል፡፡
ፊንፊኔን/አዲስ አበባን የቧንቧ ዉኃ፣የኤሌክትሪክ ኃይል ፣የባህር ዛፍ
ተክል ወደ ከተማዋ መግባት፣የዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች መከፈት፣የባቡር ሐዲድ መዘርጋትና የዉጭ ስልጣኔ መግባት አዲስ
አበባን ታዋቂ አደረጓት፡፡ እንግዲህ አዲስ አበባ እንዲህና እንዲህ እና እያለች የራሷንና በዉስጧ የፈሩትንም ይሁን የተጣበቋትን
የልደት በዓል ስታከብር ኖራለች፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህም ለይስሙላ የ125ኛ ልደት በዓሏን ልታከብር ችላ እንደነበር የቅርብ ጊዜ
ትዝታችን ነዉ፤ ዛሬም አዲስ አበባ አጼ ምኒልክ እንኳን ቢመጡ ሊለዩት የሚችሉበት ሰፈር ያለበት ሁኔታ ላይ ነዉ ያለነዉ የአዲስ
አበባ እርጅናዋ፡፡
አዲስ አበባ እንዲህ ለከተማነት ከመታጨቷ በፊት ‹‹ መካነ አራዊት
›› በመባል ትታወቅ ነበር አሁንም ቢሆን የጅቦች መንጋ እንደሆነች ሚዲያዎች አራት ኪሎ ቤተመንግስት ጋር የነበረዉን የቀድሞ ቄራ
ሰፈር እና ፊት በር በማለት የሚታወቀዉ ቦታ ጅቦች በጎዳና ላይ የሚያድሩትን እያስቸገሩ እንዳለ ሲነገር እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡
ይህ ደግሞ የሚያሳየዉ ከትናንቱ ጫካዉን አስመነጠረች እንጂ የ125 ዓመታት ሥራ አልሰራችም በማለት ያስተቻታል፡፡አዲስ አበባ!
ደርጎች በጊዜያቸዉ አዲስ አበባን ሲያንቆለጳጵሷት እንዲህ ብለዋታል
‹‹ የዙፋን አገዛዝ አስተናግዳ ያሰናበተች አዲስ አበባ በታሪክ ደማቅ የሆነዉ የኢትዮጵያ አብዮት ተቀጣጥሎ የፈነዳባትና የአብዮቱን
ቦይ ለ14ቱም ክፍላተ ሀገር ያከፋፈለች ታሪካዊት ከተማ ነች፡፡ ›› ኢህአዴጎችስ ያልን እንደሆነ ይህችን ደርጎች ታሪካዊት ያሉዋትን
አሮጊት ብለዉ አፍርሰዉ እየሰሩዋት ‹‹ልጃገረድ›› ሊያደርጓት ነዉ፤ ድንግልናሽን እኛዉ ካልወሰድን ብለዉ እንዳያስቸግሯት እንጂ፡፡
የአፍሪካ እጣ ፈንታ እንደሆነ እንግሊዞችም ጣልያኖችም አሜሪካኖችም ያሰለጠኗትን አፍሪካዊት እኛዉ ካላስረጀንሽ የሚሉት አባዜ ስለነበረባቸዉ፤
…… …
አዲስ አበባ ከአጼዉ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ብዞዎችን አስጨፍራ ተቀብላለች
አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገን ስንመለስ አዲስ አበባ ላይ ተጨፍሯል፣ ማይጨዉ ላይም ስንዘምት አስጨፍረን ተማምለን የዘመትነዉ
መነሻችን አዲስ አበባ ነበረች፣ ኃይለስላሴም ሆኑ ደርግ ዘመነ ስልጣናቸዉን አዲስ አበባ ላይ ጨፍረዉ አስጨፍረዉባታል፣ ኢህአዴግም
ለ17 ዓመታት የትጥቅ ዘመን ፍፃሜ በኋላ አዲስ አበባ ላይ ጨፍሮባታል፤ ይህች የኢትዮጵያ መናገሻ አዲስ አበባ ጭፈራ ብቻ ሳይሆን
በጭፈራ ዘርተሽ በለቅሶ ልቀሚ የተባለች ይመስል ተለቅሶባታል፡፡ ከአጼዉ ዘመን ጀምሮ በየዩኒቨርስቲዉ እና ትምህርት ቤቱ በሚነሱ
ተቃዎሞዎች ደግሞ ተለቅሶባታል፣ አጼዉ የተማሪዉን ንቅናቄ አስለቅሰዉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዉ ሲኖሩ ምን እንደሆኑ እንኳን በግልጽ
ባልታወቀ ሁኔታ የስልጣን ዘመናቸዉ ተጠናቋል፣ ደርግም የተማሪዉን ንቅናቄ አመጽ ነዉ ብሎ ችላ ቢል የተማሪዉ ንቅናቄ ወደ ግንባረነት
ተቀይሮ የተማሪዉ እና የህዝብን እንባ እግዚአብሔር አብሶት ያ ጀግንነት ከንቱ ቀርቶ በጠራራ ፀሐይ ሊፈረጥጥ ችሏል፣ ብሶት የወለደዉ
‹‹ ጀግናዉ ›› የኢህአዴግ ሰራዊትም በህዝብ ተሳትፎ ደርግን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ እንዲሁ የተለመደዉ አይቅር እያለ ከተማዋን
የለቅሶ ፍሬ እጨጂ እያላት ይገኛል፡፡
ከላይ ከጠቀስኩላችሁ ባሻገር አዲስ አበባ ‹‹ ከሚኒልክ ትምህርት ቤት
እስከ ዩኒቨርስቲ፣ ከቆሎ ትምህርት እስከ ድኅረ ምረቃ፣ ከስር መማሰና ቅጠል መበጠስ እስከ ታላቁ ሕክምና ሲካሔድ ተመልክታለች፤
›› በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦቿን እንደየአቅማቸዉ አብልታና አጠጥታ ታሳድራለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ‹‹አዲስ አበባ ጾም አይታደርባትም››
እየተባለ ከየክፍላተ አገራቱ ሰዎች ይሰደዱባታል፤ በ1979 ዓ.ም. ከ1ሚሊዮን 500ሺ ህዝብ ይዛ የነበርችዉ አዲስ አበባ ዛሬ ሶስት
እና አራት ሚሊዮን ህዝቦች ይኖሩባታል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ምግብ፣ ዉኃ፣ መጠለያ ፣ ሥራ፣ ስልክ፣ መብራት፣ትራንስፖርት፣ የጤና እንክብካቤ፣
… ወዘተ ያስፈልጋቸዋል፡፡
አዲስ አበባ ከህዝቦቿ ባሻገር የተለያዩ አገር ዜጎችን በሰላምም ሆነ
በስደት እንደመጠለያነት ታስተናግዳለች፣ የዓለም አቀፍ አገራት ኤምባሲዎች መቀመጫም ነች፣ አንድ አገር ብዙ አይነት ህዝብ ሲኖርባት
ብዙ ነገሮች እንደሚያጋጥማት ሁሉ አዲስ አበባ እንደ ላብራቶሪ አይጥ መሞከሪያ ሆናለች፤ በኮንትሮባንድ መልክ የሚመጡ እምነቶች መሸጋገሪያቸዉ
አዲስ አበባ ነበረች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ተቋማት መጠንሰሻቸዉና መጥመቂያቸዉ እና ራሳቸዉ ጠጥተዉ ሰክረዉ የገለሞቱባት ከተማ ነች፣ ብጥብጦች ቢነሱ ሰላም ቢሰፍን መነሻዉ አዲስ አበባ ነች፣ በአጠቃላይ
የዓለም ባህልና ህዝብ መናኸሪያ ነች፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ሳሎን ነች፡፡ ከአዲስ አበባ ነባራዊ ገፅታዎች ተነስተን
ትክክለኛ ገጽ ልንሰጣት አንችልም፤ ቀይ ፣ጥቁር፣ ነጭ ፣ ወይ ሌላ አይደለችም አዲስ አበባ የፀየመች ከተማ ናት ለዚህም ነዉ የአዲስ
አበባን ገፅ ‹‹የፀየሙ ገፆች ›› ለማለት የተገደድነዉ ብዙ ነገር አርፈዉባታልና፡፡
የፀየመችዉን ከተማ በክፍል ሁለት ይጠብቋት!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ