ማክሰኞ 25 ሜይ 2021

ከትንሣኤ ማግስት

 የትንሣኤ ማግስት ቀናት

በደረሰ ረታ

ሰኞ ፦ ማዕዶት መሻገር ማለፍ በሲኦል ወደ ገነት በጨለማ ወደ ብርሃን የመሻገራችን ነፍሳት ከሲኦል የመውጣታቸው መታሰቢያ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የመምጣቱ አላማ ይኸው ነውና።

በባህሪው ሞት በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት አምላክ የሞተው ለዚህ ነውና።

በዚህ በትንሣኤ ማግሥት ሰኞ በዚህ ዕለት በፋሲካችን በክርስቶስ ትንሣኤ ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከሃሳር ወደ ክብር መሻገራችንን እናስባለን፡፡


ማግሰኞ፦ ማግስተ ሰኞ ቶማስ ሲባል ቶማስ ጌታን አይቶ ማመኑ ጌታዬ አምላኬ ብሎ መመሥከሩ

እንደምናውቀው ቶማስ በጌታችንም ሆነ በእመቤታችን ትንሣኤ ወቅት በአገልግሎት ምክንያት አልነበረም ወንድሞቹ ሐዋርያት ነበሩ ስለ ትንሣኤዋ የነገሩት ነገር ግን አላመነም። በጌታ ትንሣኤ ጌታን ቢጠራጠር እርሱ ስለመሆኑ ጌታ ማረጋገጫ የሰጠው ሲሰቀል የተወጋ ጎኑን እንዲያይ ነበረ። እጁን ወደ ተቸነከረበት ቢሰደው ጣቶቹ እሳት እንዳየ ጎማ ተኮማተሩበት። አምኖም መሰከረ። ዮሐ. 20፡27-29

በዚህ እለት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለማመናችንን እንዲረዳ፣ አምነንም እንድንመሰክር እንዲረዳን እናስበዋለን።

ረቡዕ፦ አልአዛር ሲባል ጌታ አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው እናስባለን።

አልአዛርን ከሞት እንዳስነሳው ስናስብ ክርስቶስ የሞትን ስልጣን የሻረ የሕይወት ራስ፤ የመቃብርን ሥርዓት ያጠፋ ትንሣኤ፡ ድልም ያረገ ዘለአለማዊ ንጉሥ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በብዙ ጭንቅና መከራ፣ በሞትና በሕይወት መካከል ስለምንገኝ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እንደ ጉም በንኖ እየጠፋ ስለሆነ ጌታችን ለእኛም ትንሣኤ ልቡና እንዲያድለን እንለምነዋለን።


ሐሙስ፦ አዳም ሐሙስ ይባላል ለአዳም የሰጠው ተስፋና የተገባለት ኪዳን እንደተፈጸመ አዳምና ልጆቹ ነጻ እንደወጣን ይታሰብበታል።

በበለስ ምክንያት ከገነት እንደወጡ ሁሉ የአለም መድኀኒት ጌታችን ለአለመ ድህነት ከወጣንበት ገነት እንመለስ ዘንድ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ለአዳም በገባው ቃል መሠረት አድኖናልና።

አርብ ፦ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይባላል ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ መመስረቷ ይሰበካል።

በዕለት አርብ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሱ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ ቤተክርስቲያንን እንዳከበራት ይነገራል፡፡

ቤተክርስቲያን ስንል ሕንፃውን ሳይሆን አማኞችን ነው፤ ክርስቶስ ለሕንፃ አልሞተምና፡፡

ቅዳሜ፦ ቅዱሳት አንስት ሲባል የጌታን አካል ሽቱ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸው፣ ትንሳኤውን ቀድመው ማየታቸው ይሰበክባታል።

እሁድ፦ ዳግም ትንሳኤ ሲባል ለደቀ መዛሙርቱ ለ3ተኛ ጊዜ መገለጡንና ሰላምን መስበኩ ይሰበካል።

ማጠቃለያ

እንደ ክርስቲያን በአብይ ጾም ወቅት የምናሳየው መንፈሳዊ ማንነት ፍሬ የሚያፈራበት ነው። ከአብይ ጾም በኋላ ከትንሣኤው ማግሥት በቤተክርስቲያን ምሥጢር ብዙ መታሰቢያ ነገሮች አሉት አንዱ ሐምሳው ቀናት ከጾም የምንከለከልበትና አርብ እና ረቡዕ ሳይቀር የፍስክ ምግቦችን የምንመገብበት ነው።

ከዚህ በቀረው ከላይ የዘረዘርናቸው ምሥጢራትን ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያው ሳምንት ስያሜ ሰጥታ አመሥጥራ ታስተምራለች።

እኔም ከብዙ በጥቂቱ፣ ከረጅም በአጭሩ፣ አምልቼ አስፍቼ ሳይሆን በማይም አቅሜ አቅርቤያለሁ።

እንደ ክርስትናችን የሁለት ወር መንፈሳዊ ተግባራችን የሚያፈራበት ነው። ጾም፣ ጸሎታችን፣ ስግደት፣ ምጽዋታችን፣ መውደቅ መነሳታችን ያበቃለት ሳይሆን በእምነት የዘራነው መንፈሳዊ ዘር አብቦ የሚያፈራበት ነው።

ነገር ግን አብዛኞቻችን መንፈሳዊነት ያለቀ ሥጋዊነት የተጀመረ እናስመስለዋለን። ፋሲካ ሲሆን ሥጋዊነት እንዲሰለጥንብን አይደለም።

ጾም እና ንሰሐ ገብቶ ቀኖና መቀበል ቢቀር ሌሎች ተግባራት አይቀሩም። ስለዚህ የትንሣኤ ማግሥት የልቡና ትንሣኤ እንዲሆንልን እመኛለሁ።

ይቆየን።
አሜን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

የቀኝ ዐይን - ድንግል ማርያም

  የቀኝ ዐይን - ድንግል ማርያም   ( በዲ / ን ብርሃኑ አድማስ ) አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ   ምንዳቤ ወአጸባ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ውእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩ...