በይደር ያቆየነዉን ጥያቄ እንመልስ ካልን እና እንደዚህ አይነት እንደምናገባ/ለወንድም ለሴትም ያገለግላል/ ቢታወቅ እግዚአብሔር
ለአዳም ከጎኑ ሔዋንን በፈጠረ ጊዜ አዳም ባላንቀላፋ ነበር፡፡ቅዱስ ጳዉሎስም ስለ ትዳር/ጋብቻ ሲናገር " ቢቻላችሁ
…" በማለት ባላቅማማ እና አግቡ ብሎ ባስተማረ እና እሱም ባገባ ነበር፤ ነገር ግን ቅዱስ ጳዉሎስ አላገባም፡፡ ከገሚሶቹም
በቀር ከሐዋርያት አላገቡም ያገቡትንም ቢሆን ከጥቂቶቹ መልካም ሚስቶች በቀር መፅሐፍ ቅዱስ ሚስቶቻቸዉን አይጠቅስም፤አልጠቀሰምም፡፡ለምን
ካሉ ልሂቃን መልስ ይስጡበት፡፡
የሰዉ ልጅ ክፉ ሆኖ እንዳልሆነ እሙን ነዉ እኔ ክፉ ነዉ ብዬ ለመናገር ያዳግተኛል፤
እንደዉ ሌላዉ ቢቀር እነዚህ ሁለት ጥንዶች እንዃን በጓደኝነት ወቅት እንቅፋት ሲመታቸዉ እኔን ብለዉ የሚንሰፈሰፉ፣ ማዕድ እንዃን
ሲቋደሱ ቀድመዉ የማይጎርሱ፣ ትን ሲላቸዉም ሆነ ምግብ ሲያንቃቸዉ ምራቃቸዉን እንዃን ለመስጠት ወደ ኋላ የማይሉ፣ ያፈለገዉን ያህል
ቀጠሮ ቢያረፍዱ በትዕግሥት የሚጠብቁ ፣ … ሁሉንም ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል በወዘተ መገላገል ሳይሻል አይቀርም፤ ስለሰዉ ልጅ
ጥሩነት ለመግለፅ በቂ ናቸዉና (ለማያምን ግን ሺም ቢዘረዘር አያሳምነዉም)፡፡ ከትዳር ማግስት ግን እነዚያ ሃሜትም ምክርም የማይሰሙ
ጥንዶች ጆሮአቸዉ በኦዙን የሳሳ ይመስል ሽንቁር ይሆናል፡፡ ሆድ ይብሰዋል፣ ቶሎ ይከፋዋል፣ ቂም ይቋጥራል፣ ወሬ ይሰማል፣ ነገር
ይጠመዝዛል፣ በአጠቃላይ ማንነቱ ላይ የሆነ ነገር ዞር ይለበታል፡፡ አጋሩን/ሚስቱን እንቅፋት ሲመታት እያየሽ አትሄጂም ምን ወሬ
ታያለሽ፣ምግብ ሲያንቃት ቀስ ብለሽ አትበይም ምን ያጣድፍሻል ዉድድር የለብሽ እያለ ይነቅፋታል፣እሷም አባወራን የሚያህል ነገር ከዉጭ
ቀርቶ ሲያመሽ ስለጤንነቱ ሳይሆን ቅናት ፀጉሯን አቁሞት ሰላም አመሸህ እንደማለት የት አመሸህ ብላ በነገር ትቀበለዋለች፣ ከመነጋገር
በግል መወሰን ይጀምራሉ ይህ ነገራቸዉ ለብቻ ወስኖ እስከማርገዝ አልፎተርፎም ለብቻ የህክምና ክትትል ይጀመራል በአጋጣሚ ሃኪም ባለቤትሽስ
ሲላት አልሰማም ለምን ከተባለች አርግዤ አምጬ የምወልደዉ እኔ እሱ ምን አገባዉ ድረስ ይዘልቃል፤ ….
ሳምንቱ ከምኔዉ አልቆ/ዕለቱ ከምኔዉ መሽቶ
በተገናኘን እንዳላልን እና ቀኑ እንዳላለቀብን ሰወች ወደ
ትዳር ሲገቡ ለአፍታም እቤት የማይገኙ አባወራዎች፣ ድሮ አንዲት ቅዳሜ / ዕሁድ ለስንት ነገር እንዳልበቃች ትዳር ዉስጥ ሲገቡ ግን
በፀጉር ቤት ሰበብ ወጥታ የማትመለስ ሚስት … ትዳርን መልኩን እያፀየመዉ ስሙን እያጎደፈዉ ይታያል፡፡ ይህ ከሰዉ ባህሪ እንጂ ትዳር
ይዞት የሚመጣ ጉዳይ እንዳልሆነ እሙን ነዉ …
ለምን ነዉ ሰወች በትዳር ዉስጥ ሰላም/ደስታ የሚያጡት?
1.
ስልቹ መሆናችን ፡- ከጋብቻ አስቀድሞ በሳምንት ዉስጥ / በቀን ዉስጥ ስለምንገናኝ የምናጠነጥነዉ አስደሳች ነገሮች ላይ ብቻ ስለሆነ
የምንተዋወቀዉ እናም ወደ ትዳር ሲመጣ ግን ቀን ከሌሊት ያለማቋረጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ዉስጥ ስለምንቆይ እና አዲስ ነገር ሳንፈጥር
አዲስ ነገር ብቻ ስለምንጠብቅና ስለማይኖር ስልቹ እንሆናለን፡፡
2.
ትዳር የሚያጋራን የጋራ ጉዳይ ስላለ ፡- ትዳር አብሮነት እንደመሆኑ መጠን በጋራ የምናደርጋቸዉ እና የምንጠቀማቸዉ ነገሮች
ይከሰታሉ፤ መኝታ ከመጋራት አንስቶ ወጪን እስከመጋራት የሚደርስ ነገሮች ስላሉት እነዚህ ነገሮች ደግሞ ሁለቱን ማዕከል የሚያደርግ
እንጂ የአንዱን ፍላጎት ብቻ የሚያሟላበት ነገር ስለሌለ ይህ ደግሞ ለማንፈልገዉ ነገር ያስገዛናልና፡፡
3.
ከሁለት ዓለም የመጡ ሰወች የሚመሰርቱት አንድነት/ህብረት ስለሆነ ፡- ሁሉም ነገር የመላመድ ዉጤት እንደመሆኑ መጠን የታገሰ
ከሚስቱ ይወልዳል እንዲባል ትዕግስት የሚያሻዉ ግንኙነት ስለሆነ በመላመድ ቤቱን/ የትዳር ህይወትን
በጋራ ሊመሩት ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሰላምን የሚነጥቅ … ይሆናል፡፡
4.
የአመራር ክህሎት ስለሚጠይቅ ፡-መሪነት የሚጀምርበት ትልቁ ተቋም ትዳር/ ቤተሰብ ስለሆነ የአመራር ክህሎት የሚጠይቅ ስፍራ ነዉ፤ ክህሎቱ ከሌለን
የምንለቅመዉ ፍሬ የዘራነዉን ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ትዳር አገርን ለመምራት መነሻ ስፍራዉ ነዉ፤ መሪነት የሚጀምረዉ ከቤተሰብ ስለሆነ፡፡
5.
ራስ ወዳድ መሆናችን ፡- ትዳር ማለት አንተ ትብስ
አንቺ ትብሽ ተብሎ የሚኖርበት እንጂ ራስ ወዳድነት የሚነግስበት ተቋም አይደለም፡፡ ይህ ሲከሰት መገለጫዉ ስላልሆነ በአሉታዊ ተፅዕኖ
ስር መዉደቃችን አይቀሬ ነዉ፡፡
6.
በጥቂቱ የማንረካ መሆናችን፡- ፍላጎት ማብቂያ ስለሌለዉ
በጓደኝነት ወቅት ሲያስደስተን እና ወደ ትዳር እንድናመራ መንገድ ቀያሽ እንዳልነበረ ወደ ትዳር ስንገባ ግን አስቀድሞ በነበረዉ
መንገድ መቀጠሉ በሁለቱም ጥንዶች የማይደገፍ ይሆናል፡፡ ህይወታቸዉም ርካታ ያጣል ነገሮች ሁሉ ጣእም ያጣል፣ አዲስ ነገር መፍጠር
ግዴታ ይሆናል ዘወትር መትጋት ይጠይቃል፡፡
7.
የመነጋገር ባህላችን አለመዳበር፡- በትዳር ዉስጥ
በጋራ የሚተገበር/የሚወሰን ብዙ ጉዳዮች እንደመኖራቸዉ መጠን መነጋገር ይጠይቃል ባህላችን ደግሞ በዚህ እስከዚህም ነዉ ስለዚህ ሰላም
እየደፈረሰ ይመጣል፡፡
8.
የምንጠብቀዉ እና የምናገኘዉ ነገር መለያየት፡-
በፍቅር ዉስጥ የምናየዉን ነገር በሰፊዉ ስለምንጠብቅ ያሰብነዉን ደግሞ ስናጣ ደስታችንን እንነጠቃለን፤ ከዚህ ይልቅ አብዝተን የጎደለዉን
ነገር በጋራ ለማምጣት ብንጥር የተሸለ ነዉ፡፡
9.
የሰዉ ጣልቃ ገብነት፡- ከባህላችንም ሆነ ከአኗኗራችን
ስንነሳ ተሰባስበን በአንድነት መኖር የለመድን ማህበረሰብ እንደመሆናችን አንፃር ትዳርንም ለተጋቢዎች እንደመተዉ እኛም ጣልቃ ካለገባን
በማለት የጥንዶችን ደስታ የምናጨናግፍ ብዙ ነን፡፡
10.
ዝግጅት አለመኖር፡- ቅድመ ጋብቻም ሆነ ድህረ ጋብቻ
ስላሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ከማህበረሰቡም ሆነ ከቤተሰብ የምንማረዉ በተቋምም ደረጃ በትዳር ላይ ትምህርት የሚሰጥ አለመኖሩ/አለመስፋፋቱ
ከመቋቋም ይልቅ ለድንጋጤ ቅርብ ነን፤ ይህ ደግሞ አንዱ እና ዋናዉ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ነዉ፡፡
11.
ያለዉዴታ በተፅዕኖ ዉስጥ ወደ ትዳር መግባት፡-
ዝግጁ ሳንሆንና ፈቃደኞች ሳንሆን በቤተሰብ (በዕድሜ የገፉ ቤተሰቦች ካሉ በተለይ አንድ ከሆንን ልጄ ዓለምህን ሳላይ እንዳልሞት
የሚል ስብከት ካለ) እና በጓደኛ (ምክር እና ጓደኞች ሁሉ አግብተዉ ከሆነ ቆመን የምንቀር እየመሰለን )አለበለዚያም በአንደኛዉ
ወገን ፍላጎት ብቻ በግፊት መግባት፤ እንደዉም ይህ ሁኔታ አሁን አሁን እየቀነሰ ቢመጣም በጓደኛ ተፅዕኖ ትዳር መመስረት አልፎ አልፎ
ይታያል፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ ጥቅምን/ እዉቅናን/ ስህተትን ለመሸፈኛ በማድረግ (ከጋብቻ በፊት እርግዝና ሲፈጠር) ትዳር እየተመሰረተ
ያለበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ፡፡
12.
ፉኩኩር፡- የፉኩኩር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ
እልክ በመገባባት ትዳርን ለአደጋ የሚያጋልጡ ባለትዳሮች መጨረሻቸዉ ሰላም የራቀዉ ግንኙነት ይሆናል፡፡
13.
ማሰተዳደር ያለመቻል፡- ሰላም ከሚጠፋበት አንዱና
ዋነኛዉ የሰዉ ልጅ ትዳር ከመሰረት ምንም እንኳን ዋናዉ ፍቅር ነዉ ቢባልም ቅሉ ከአገራችን ባህል አንፃር ወንዱ ቤቱን ማስተዳደር
ካልቻለ አደጋ አለዉ፤ በትንሽ ፍቅር የተጀመረ ትዳር ማስተዳደር አለመቻል በከፍተኛ ልዩነት ሰላምን ይነሳል፡፡
14.
እንዲህና እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ወዘተ …
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ