ሐሙስ 29 ማርች 2012

‘’Disqualify’’


Disqualify  የሚለው ቃል የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ‘’verb’’ ወይም ግስ ብለን የምንጠራው ሲሆን መዝገበ ቃላት ‘’to put out of a competition’’  ወይም ‘’to make unfit for some purpose’’ብሎ ይፈታዋል በመጠኑ ወደ አማርኛ ሳንመልሰው ‘’የማይመጥን፣ከጨዋታ ውጭ ማድረግ፣…… ወዘተ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡
    ይህንን  ነገር ጫር ጫር  ለማድረግ አንድ ነገር አጋጠመኝ ገጠመኙ እንዲህ ነው ‘’ታቦት ከመንበሩ ሰው ከሃገሩ የሚወጣው ችግር ሲኖር ነው’’ ይላሉ የአክሱም ሰዎች እናም አንዲት እህቴ  ኑሮ ሲከብዳት ሥራ ካለዘመድ፣ ካለ እጅ መንሻ፣ ሴትነትን ካልገበሩ በቀር፣ (እንዲያውም በአንድ በአገራችን ባለ ትልቅ ተቋም B.P.R ወይም Transformation የሚባለው ነገር ሲሰራ ለምደባ እና ለሹመት እንደ መወጣጫ አገልግሎ ነበር አሉ) ብቻ ምን አለፋችሁ ለብዙ ዓመታት ለረጅም ወራት ብዙዎች ሥር አጥተው እቤት አንደሚቀመጡት ሥራ አጣች፣እቤት ተቀመጠች፡፡’’ በእንቅርት ላይ…. ‘’ እንደሚባለው ሥራ በማጣት ላይ ይህችን አገር ጠላች፡፡  መጥላት በአገራችን በሰፈነው ዲሞክራሲያዊ መብት የተለገሳት ነውና፡፡  እንኳን እርሷ ሥንቶች ሄደው የለ? እንኳን እርሷ አንድ ግለሰብ ይቅርና ቱባ ቱባ የአገሪቱን ሥልጣን ተሸክመው አገርና ህዝብ ሲመሩ የነበሩትስ ጠልተው ወይ ተጣልተው  ሄደው የለ? ታዲያ ይመሯትና ያስተዳድሯት የነበሩትን ታማኝ የአገሯን ባለሥልጣናት ተከትላ ብትሄድ ምኑ ነው ክፋቱ? ወንጀል ሰርታ ለመሰወር፣ የአገሪቱን ሃብት ንብረት መዝብራ ለመደበቅ አስካልሄደች ድረስ፡፡
     ሊቁ ወደ  ጥንተ ነገራችን እንመለስ እንዳለው ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና  በቃ ሥራ አጣች አገር ጠላች ሥደት አማራት ይቅርታ ከአገር ወጥታ ሌላ አገር ሄዳ ሥራ ለመፈለግ  ተመኘች ሰው አገር ሄደች ከመሄዷ በፊት ግን እንዲህ ሆነ እርሷ ለመሄድ ተመኘች ፣ ቤተሰብ መክራ ወዳጅ ዘመድ ወንድም እህት ገንዘብ አሰባስባ፣ደላላ ተፈለገ፣ /ተገኘ/ ኤምባሲ ተሄደ፣ ቪዛ ተመታ፣ደላላ ብሬን ክፈሉኝ አለ ከአገር የምትወጣበት ቪዛ ማግኛ ሳይሆን ከአገር  ለመውጣት የምታቆራርጥበት የመኪና መግዣ የሚያክል  ዋጋ ጠየቀ፣ አለመግባባት ተፈጠረ፣ ፓስፓርቷን ነጥቋት ሄደ፣ ሽምግልና ተጀመረ እንዲህ አለ፡፡……’’የምላትን ገንዘብ አስካልከፈለችኝ ድረስ የትም አትሄድም ፓስፓርቷን  አቃጥለዋለው ከዚህ በኃላ  ወደውጭ አገር የመሄድ ሙከራ እንዳታደርግ  የእርሷን ጉዳይ Disqualify አደርገዋለሁ አለ፡፡’’ እጅግ በጣም በማን አለብኝነት፣ በትቢዕት፣ ከ’ኔ ወዲያ አድራጊ ፈጣሪ የለም በሚል ሥሜት፣….. ምን አለፋችሁ  ብዙ ብዙ  ነገር ሆነ………..ግን ሄደች የልቧ ደረሰ እንባ እራጭታን ተሸኘች፡፡
     ነገሩ ወዲህ ነው አስኪ በህይወታችን ውሰጥ ሰዎች በሥልጣናቸው፣ ሰው በማወቃቸው፣ ገንዘብ ሥላላቸው፣ አካሄዱን ሥለሚያውቁበት፣ ብቻ ምናለፋችሁ በሆነ በሆነ መንገድ አድርገው ይገባሉ ገብተዋል ለመግባት አድብተዋል፡፡  ግን! ግን ይህን ለማድረግ እነርሱ ማን ናቸው? እነርሱ በኛ ህይውት ላይ ይህንን ሲያደርጉ መብት ካላቸው በእኛ ላይ እንዳይደረግ ፍትህ የለም እንዴ? ምን ይደረግ ‘’ገንዘብ ሲናገር ፍትህ ዳጥ’’ ይላል ተብሎ የለ፡፡
    አንድ ነገር ልበላችሁ ሰዎች ብዙ ነገር ሆነው ይሆናል ለመከላከል ብዙ ደክመው ድካማቸው ከንቱ ሆኖ ይሆናል እናንተ ግን አትሸነፋ ብዙዎች ታላላቅ ብለን ታሪካቸውን  የምንዘክርላቸው ታዋቂ  ባለሃብቶች፣ ምሁራን፣ቅዱሳን፣……. ከብዙ መውደቅ መነሳት በኃላ፣ ከብዙ ሽንፈት  በኃላ፣ ከብዙ መንገላታት  በኃላ ነውና ለዚህ የበቁት ለውድቀታችን መንስኤ የሚሆነው  መጀመሪያ የራሳችን መውደቅ ስለሆነ ጥንቃቄ እናድርግ ራሳችንን ሥንጥል ነውና ሰዎች እኛን ለመጣል የሚበረቱት፣ በደካማ ጐኖቻችን ሥለሆነ እየገቡ የሚጥሉን እጅግም ራሳችንን ለጠላቶቻችን ክፍት እናድርገው ማንነታችንን ይጫወቱበታልና እንቁዎቻችሁን በእርያዎች /ዓሣማዎች/ ፊት አታስቀምጡት እንዳይስብሩባችሁ’’ እንዲል እንቁ ማንነታችንን እንጠብቅ ብዙዎች በዚህ የተነሳ  ከሥራ ገበታቸው፣ ከሚያምር ትዳራቸው፣ ተምረው ይመጥናሉ  ተብለው ካገኙት ሥልጣን /የሥራ ደረጃ/ ከክብራቸው (ከድንግልናቸው)፣ በሰው ዘንድ ተዓማኒ ከመሆናቸው፣…… ወዘተ Disqualify ተደርገዋል ሊደረጉ ተዝቶባቸዋል፣ እየተደባባቸው ይገኛል፡፡ ግን ለምን?
    ወደኃላ ተመልሰን ታሪኩን ሥንዳስስ ያ ሰው ፓስፓርቷን ቪዛዋን…… እንዲያውም ይባስ ብላ የትም አገር እንዳትሄድ ጭምር ብሎ ሲዝት በየቦታው በየስራ ክፍሉ ለእውነት የቆመ የለም?  ፍትህስ የለም?  እውነትስ ወደየት ሄደች?  ልብ አርጉ ይህ ሰው አንድ ብቻውን ነው ብዙ ኤምባሲዎችን የመንግሥት ተቋማትን /ኤሜግሪሽንን/ ጨምሮ ማለት ነው የሚያምሰው እርሱን የመሰሉ ህብረተሰቡን የሚያውኩ ተቋማትን ለመጣልና አላማቸውን ለማሳት ባለሥልጣናትን ለማሰናከል ላይ ታች የሚሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

    ዛሬ በየማረሚያ ቤቶች /እስር ቤቶች/ ሥንት ባለስልጣናት የኃላፊነት ቦታ ላይ ሲሰሩ የነበሩ በንፅህና ህዝቡንና መንግሥትን ሲያገለግሉ ከነበሩበት እነዚህ ሰዎች እየገቡ ክፋ ዘር ዘርተውባቸው ጉድ የሰሯቸው ገሚሶችም እንሰሳትን ጨው በማላስ ወደ መታረጃው እንዲወስዷቸው እንዲሁ ጨው የተባለ ጥቅምን /ገንዘብ/፣ ውዳሴን፣ዝናን ወዘተ በማቅመስ ወደ እስር ቤት ያስወረወሯቸው ዘመድ፣ የቅርብ ወዳጅ በመምሰል የሃሰት ፈገግታቸውን በማሳየት እየሳቁ የገደሏቸው ቤተሰባቸውን የበተኑባቸው፡፡
     አንድ ነገር አጥብቄ መናገር እፈልጋለሁ የትም ይሁን የት በቀበሌ ከጥበቃ  እስከ  ቀበሌው ሊቀመንበር መታወቂያ አንሰጥም፣ የቀበሌ ቤት አንሰጣችሁም ጉዳያችሁን አንፈፅምላችሁም ብሎ ጉዳያችንን Disqualify የሚያደርጉብንን፣ በየመሥሪያ ቤታችን  የዓመት ፈቃድ (ዕረፍት) ከመስጠት እስከ ዕድገትና ዝውውራችን ላይ የሚቀልዱትን፣ሆስፒታል ሄደን ከካርድ ክፍል እስከ ሐኪሙና የመድኃኒት ወይም ላብራቶሪ ክፍል ድረስ፣ በትምህርት ቤት ከዩኒት ሊደር፣መምህር ዳይሬክተር ድረስ ፣በዕድር፣በዕቁብ፣ በትዳር ውሰጥ የእኛን ጉዳይ Disqualify በማድረግ ሽባ  ሊያደርጉ  አሰፍሥፈው የሚጠብቁትን በቃ ልንላቸው ይገባናል፡፡ ይህንን ለማስከበር  ከተቋቋሙ የፀጥታ ኃይሎች፣ የሰብዓዊ መብት፣ ዕንባ ጠባቂ ፣ ፀረ-ሙስና ኮምሽን፣በአጠቃላይ ከመንግሥት ጐን ልንቆም ይገባናል፡፡ ለመብታችን ዘብ እንቁም  እንዚህን ሰዎች እናጋልጥ ችግሩን ከምንጩ እናድርቅ ተዋናዬችም ካለን እንታቀብ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...