በሰማይም በምድርም ያሉ ደራሲያን ተወዳድረው በዓለም ላይ በተለያዩ ውድድሮች ተሸላሚዎች እንዳሉት ሁሉ ደራሲው በኪነጥበቡ ዘርፍ የኦስካር ተሻሊሚ ሆነ ከሽልማቶች በተጨማሪ ከሰማይ ዓለም ሠማያዊውን ዓለም ይጉበኝ ዘንድ ዕድሉን አገኘ፡፡
ለመጐበኘት አስጐብኚ ያሻው ነበርና ልዑል እግዚአብሔር ከመላዕክት አንዱን ላከለት መልዐኩም በፍጥነት ክንፏን እያማታ እየበረረ ምድርን እየባረከ ፈጣሪውን እያመሰገነ ወደ ደራሲው ዘንድ እየገሰገሰ መጣ፡፡ ኦ! አንተ ደራሲ ሰላም ላንተ ይሁን! ቃላትን አስውበው አቀናብረው ለሚፅፍ እጆችህ ያለመታከት የቃላትህን ቅንብር አይተው ለይተው ለሚያነቡና ለሚያርሙ ዓይኖችህ አምልተው አስፍተው ለሚያገናዝቡ ህሊናዎችህ በፀጋ ያገኘኃቸው ብሩህ ልቡናዎችህ ተቀድተው ተስፍርው ለማያልቁ የዕውቀት መዝገቦችህ ክብር ውዳሴ ሊነሱና ለፈጠራቸው ለአምላኬ ይሁን፡፡ እነሆ ፈጣሪዬ ወዳንተ ሰደኝ ፈጥኜ መጠቻለሁና ሰላም ላንተ ይሁን እንደምን ሰነበትክ ከልቡናህ ምንጭ የፈለቁ በብዕርህ ጠብታ የከተሙት የኀሊናህ ዓለሞችስ እንደምን ሰነበቱ? አንተሰ ድካም እርጅና ሳይረቱህ ስንፍና እጅህንና ዓይንህን ሳያዝላቸው እንደምን እዚህ ደረስህ ከዘረጋህ ሳታጥፍ ካጠፍክ ሳትዘረጋ በትጋት የዕድሜህን እኩሌታ በማንበብና በመፃፍ ለዚህ ዓለም ባበረከትከው እንዲሁም ተወዳድረህ አቻ በማጣት ባሸንፍከው ሙያህ የሰማዩን ዓለም ትቃኝ ዘንድ ወደ አንት መጥቻለሁና በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ እባክህ ተከተለኝ?
ከሙሉ ጨረቃ ብርሃን ይልቅ ገፃችህ እጅግ የተዋቡ ከከዋክብት ግርማ ይልቅ ግርማህ እጅግ የሚያስፈራ ከአዕዋፍ የንጋት ዜማ ይልቅ የድምፅህ ተጐድጓዳማነት እጅጉን የልብን በር የሚስብር መአዛዎችህ ከፅጌራዳ መአዛ ይልቅ ድምቀትህ ከመስከረም አደይ አበባ እጅጉን የፈካው አንተ ግሩመ ዕፁብ ድንቅ የሆንክ አንተ ሆይ ከወደየት መጣህ አመጣጥህስ እንደምን ነው እንዲህ የከበደህ የከበርህ የተፈራህ ሆነህ ሳለህ ወደኔ መምጣትህ ሥለምን ነው ማን ነህና ማንስ ብዬ ልጥራህ አኗኗርህ ከየት አፈጣጠጠርህስ ከምንድን ነው ምድራዊ ነህን ወይስ ሰማያዊ አባክህ የዓመታት ድካሜና ልፋቴ ያላዛሉት ጉልበቴን ግርማ ሞገስህ መቅኔዬን እያሳጡኝ ነውና ጉልበቴም ብርክ ብርክ ብሏልና የልብ ምቴም እየተዛባ ነውና እባክህ ንገረኝ ሥለምን ነገር መጣህ መደየትስ ልትወሰደኝ ተላክህ::
አትፍራ አትደንገጥ ላፅናናህ ላበረታህ ሽክምህን ላቀልልህ እንጂ ለከፋ ነገር ወደአንተ አልተላኩምና በኦሪትም በአዲስ ኪዳንም ሥራዬ ማፅናናት ነውና ማነህ ላልክኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሂድ ሲለኝ የምሄድ ና ሲለኝ የምመጣ አድርግ ያለኝን የማደረግ አታድርግ ያለኝንም እንዲሁ የምተው ባሪያው የእግዚአብሔር መልዐክ ነኝ አሁንም ወደ አንተ ዘንድ የመጣሁት ልፍትህንና ድካምህን ፈጣሪ ተመልክቶ የዕድሜህን አጋማሽ በደራሲነት አሳልፈሃልና የድካምህን ጊዜ ሊያስረሳህ ከድካምህ ሊያበረታህ የሚችል ጊዜን እንድታሳልፍ በሰማይ ካሉትመ ቀደምት እኩሌታዎችህ ጋርም እንድትተዋወቅና ልምድም እንድትካፈል ሲል እድሉን ስለሰጠህ ልወስድህ ወዳንተ መጥቻለሁ፡፡
ሳይገባኝ እኔን ባሪያውን ስለሳበኝ ከውርደቴ አንስቶ ከፍ ከፍ ስላደረገኝ ከሠው አልቆ ይህንን ዕድል ስለሰጠኝ ሁሉን ለሚገዛ ሁሉ በእጁ ላለ ሁሉ በእርሱ ፈቃድ ለሚሆን ለፈጣሪዬ ክብር ምስጋና ውዳሴና አምልኮ ለርሱ ይሁን ለአንተም እንዲሁ ምስጋና ይሁን፡፡
ደራሲውም ብራናውን ጠቅሎ የቀለም ቀንዱንና ብዕሩን ሸክፎ ቤተሰቦቹን በዚህ ዋሉ በዚህ እደሩ ሳይላቸው በዕለቱ ተነስቶ ጉዞውን ከመልዐኩ ጋር አደረገ መልአኩም ደመና ጠቅሶ ሰረገላውን ጭኖ ጉዞውን ወደሰማየ ሰማያት ከእግዚአብሔር ዘንድ አደረገ፡፡
ከምድር ከፍ ከፍ እያሉ ምድርን እየራቁ ወደ ሰማይ እየቀረቡ ደመናን እየሰነጠቁ የምድርን አፈጣጠር እያደነቁ ስለሰማይ እያወሩ እያመሰጠሩ እየተጫወቱ ገሰገሱ ደራሲው ከአዕምሮው በላይ የሆነበትን እየጠየቁ መልዐኩ ጥያቄውን እየመለሰ አዲስ ነገር ሲኖር መልዐኩ እየነገረው አያስተዋወቀው መንግዳቸውን ይጓዙ ጀመር፡፡ ደራሲው የምድርን ስፋት ሲያስበው ተሰፍሮ ተለክቶ የማያልቅ ይመስለው እንዳልነበር ከምድር እየራቀ ለሰማይ እየቀረበ ምድር በፊቱ እያነሰ ፍጡር ኢምንት (የሰናፍጭ ቅንጣት) እያከሉበት ተመለከተ ያንን የሚያክል አገር ያንን ሰፊ ባህር ምን ጠቀለለው ምንስ አሳነሰው እያለ ግራ በመጋባት ይመለከት አፈጣጠሩንም ያስላስል ገባ፡፡
መልዐኩ ደራሲውን ቢመለከተው ተመስጦ አገኘው ምንስ እያሰብክ በምንስ እየተመሰጥህ ትገኛለህ አለው፡፡ የማውቀው የምድር ስፋቱ የባህር ጥልቀቱ በፊቴ አንሶ ሳገኘው አፈጣጠሩ እና አኗኗሩ ደነቀኝ እንደምን ተፈጠረ ፍያልኩ እያስብኩ እየተደነቅሁ ነው አለው፡፡
መልዐኩም ስለምድር አፈጣጠር እንዲህ ሲለ ነገረው ‘’እግዚአብሔር ሥነ-ፍጥረትን መፍጠር ሲጀምር ብዙውን አንድ ብዙውን አንድ እያለ ሃያ ሁለት ሥነ-ፍጥረት በሃያ ሁለት አርዕስት አበው ምሳሌ ፈጥሯል ከሁሉ አስቀድሞ ግን ሰማይና ምድር ተፈጥረዋል እግንዲህ ምድር አሁን የምትደነቅባት ሰማይ ደግሞ በኃላ የምናያት ሲሆኑ አሁን እያየኃት ያለችው ምድር የደረቀነት፣የጨለማነት እና የቀዝቃዝነት ባህሪ ሲኖራት ለሰው ልጅ መኖሪያነት ተፈጥራለች ከእግዚአብሔር ጋርም ትመሳሰላለች ‘’እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች’’ እንዲል መዝሙረ ዳዊት 84 12
እንግዲህ በቀረው ጊዜአችን የመላእክትን ዓለም፣ የመላእክትን ከተማ፣ መኖሪያ ሥፍራችንን አሥጐበኝሃለው ጥቂት ቀናትን በኛ ከተማ በመቆየት ከጐበኝህ በኃላ ቀጣዩን ቀናተ ደግሞ ገነትን እና ሲኦልን እንደቅደም ተከተላቸው እንጐበኛለን፡፡ በገነትና በሲኦል ቆይታችን በቀደሙት ጊዜያት በተመሳሳይ ሙያ ላይ (በድርሰት) ሲሳተፍ የነበሩትን በአካል የምታውቃቸውን በታሪክ የሰማሃቸውን ነገር ግን በአፀደ ነፍስ የሌሉትንና ዓረፍተ ዘመን ገቷቸው የተለዩህን የመመልከት ዕድሉን ልታገኝ ትችላለህ እንዲሁም ሌሎችን ታላላቅ ሰዎች፣ ሳይንትስቶች፣ባለስልጣናት፣ባለፀጐችን፣ድሆችን፣ፃድቃንና ኃጥአንን በሙሉ ዓለም ከተፈጠረ አንስቶ እስከዚህ ድረስ በአፀደ ሥጋ ከተሰወሩት በቀር የሞቱትን በአጠቃላይ እንጐበኛቸዋልን፡፡ በማለት መልዐዙ የነበረው የማስተዋወቅ ሥራ አጠናቀቀ ደራሲው በብዕር ሊያስቀምጠው በኀሊናው ከሚያወጣውና ከሚያወርደው በላይ ስለሆነበት በዝምታ የአዎንታ ምላሹን አንገቱን ላይና ታች በመነቅነቅ አፀፋውን መለሰ ምድራዊው አለቀ ጉዘ ወደ ሰማይ ምደራዊው ከሰማያዊው የእግዚአብሔር መልዐክ ጋር የመጀመሪያውን የደራሲውን እና የመልአኩን ግንኙነት እዚህ ላይ በማቆም በቀጣዩ ምዕራፍ እስከምንገናኛ ቸር ይግጠመን፡፡