የመስቀሉ ነገር
ደረሰ ረታ
16/1/2013
(ደመራ)
በንግሥት እሌኒ ትእዛዝ መሰረት መስቀሉን ለዘመናት ከተቀበረበት የቆሻሻ ክምር/ተራራ ሥር ጎልጎታ ከኢየሩሳሌም በብዙ መከራ እና ፍለጋ አግኝታ እስክታስወጣው (ከመስከረም አሥራ ሰባት እስከ መጋቢት አሥር) ቀን ድረስ የመስቀሉ ሃይል አይታወቅም ነበር።
መስቀሉ አስቀድሞ ከባድ ጥፋት/ወንጀል የፈጸሙ ሰወች ምድርን እንዳያረክሱ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብለው በሞት የሚቀጡበት የተመሳቀለ ከእንጨት የሚሰራ ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስም ክብር ይግባውና ከወንጀለኞቹ እንደ አንዱ ተቆጥሮ ተሰቀለበት። በእለተ አርብ መጋቢት ሃያ ሰባት ቀን በስድስት ሰአት በከበረ እጸ መስቀል ላይ ሰቀሉት። ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፣ሮዳስ በሚባሉ ችንካሮች ቸነከሩት። እንደ ወንበዴ ሊቆጥሩት ንጹሁን በወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ።
የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ያድነው ዘንድ በእንጨት መስቀል ተሰቀለ። መከራን በሥጋው ተቀበለ።
የወንበዴዎች መቅጫ መስቀል በመለኮት ደም ከበረ።
ብዙ ተአምራትን ሰራ፤ አይሁድንም አሳፈረ። ፈርተው ደነገጡ።
ከዚህ በኋላ የመስቀሉ ነገር የአደባባይ ምሥጢር ሆነ።
አይሁድ በቅናት አይናቸው ስለቀላ የማዳኑን ሃይል ለመደበቅ በደላቸውንም ለመሸሸግ ያንን የወንበዴ መቅጫ የተመሳቀለ እንጨት/መስቀል በመለኮት ደም ከብሯልና ክብሩን ለመሸሸግ ወስደው ከምድር በታች ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረው ቀበሩት። የወንበዴዎቹንም መስቀል ከላይ አደረጉበት። እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ (327አ.ም) ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆሻሻ ተከምሮበት ለብዙ ዘመናት ለረጅም ወራት ተደብቆ ኖሯል።
አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ቆሻሻ ደፉበት፣ የቆሻሻውም ብዛት ተራራ ሰራበት።
በመስቀሉ ልቧ የተነካ ንግሥት (ንግሥት እሌኒ) ደመራ አስደምራ መስከረም አስራ ስድስት በእጣን ጢስ እየተመራች የተቀበረውን መሥቀል ከተቀበረበት ከምድር ልብ አወጣች።
በአጼ ዳዊት ዘመነ ንግሥና ታስቦ እርሳቸው አረፍተ ዘመን ሲገታቸው በአጼ ዘርኣያቆብ ዘመን ኢትዮጵያ የግማደ መስቀሉ ባለቤት ሆነች።
የትናንቷ ኢትዮጵያ፣ የትናንት ኢትዮጵያውያን፣ የትናንት እናቶች(ሴቶች)፣ የትናንት መሪዎች ይህን ተግባር ሲፈጽሙ የዛሬዎቹ ግን ከቤተክህነት እስከ ቤተመንግሥት ለዚህ ዘመን ለዚያውም ለዚህ አገር እና ትውልድ የማይመጥን ተግባር ይፈጽማሉ።
ሆሳእና "አሁን አድን" የሚል ስያሜን ይዛ አሁን ለክርስቲያኑ ፍትህ ነፍጋለች፣ ከተማዋ ከካህን ስያሜዋን ያገኘች ብትሆንም ካህን ገፊ ሆናለች፣ ከተማዋ ለምህረት ይሁን ለመአት እሳት ይዘንብባት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ሆሳእና የጌታ መገለጥ የታየበት በአል ቢሆንም ኢትዮጵያዊቷ ሆሳእና ግን ከክቡሩ የሰው ልጅ የጥምቀት እና የመስቀል ደመራን ማክበሪያ ሥፍራ ለከብት ማቆሚያ ተሰጥቷል።
የእንስሳት ክብር ከሰው/ከክርስቲያን ክብር ልቋል።
ናዝሬት (አዳማ)፣ ደብረዘይት (ቢሾፉቱ)፣ ሞጆ፣ስልጤ፣ እና ሌሎች ክልልም እንዲሁ እየቀጠሉበት ነው። የቤተክርስቲያንን ጥላቻ የመንግሥትን ሥልጣን ተገን አድርጎ ግለሰቦች ጫና ሆነዋል። ይህ ጥላቻ ጅማ፣ ጅግጅጋ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አሩሲ፣ አሰላ፣ መተከል ወዘተ ላይ አብያተክርስቲያናት ተቃጥለዋል ክርስቲያኖች ተሰውተዋል፤ ሐብት ንብረቶች ወድመዋል። የመንግሥት ተሿሚዎች እንደገና መልሰው ክርስቲያኑን በመግለጫ አስፈራርተዋል። የጸጥታ አካላት ቆመው ባለበት ሥፍራ የተደራጁ ጽንፈኞች አካላዊ እና ስነልቡናዊ ጥቃት ሲፈጸሙ እያየን ነው። መንግሥት ጥቃቱን ከመከላከል ይልቅ ለአጥቂዎች ሽፋን እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
በአስሩም ክልሎች በሁለቱም የፌደራል ከተሞች በሁሉም ወረዳና ቀበሌ፣ በሁሉም የግልና የመንግሥት ተቋማት ብልሹ አሰራር እና አመራር፣ በግልና በመንግሥት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መስቀሉ ተቀብሯል። የመስቀሉ አዳኝነት፣ የመስቀሉ ሃይል፣ ተደብቋል። ቆሻሻው (ምንዝር፣ ሙስና፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግብረ ሰዶም፣ የበላነት መንፈስ፣ የተተኪነት መንፈስ፣) ተከምሮበታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እነርሱም (በሽንገላም ቢሆን) እንደሚሉት እኛም እንደምናምነው ሁሉን አቻችላ እና እኩል አድርጋ ከማእዷ የምታጋራ አገርም እናትም ጭምር ናት።
ይህች ሥንዱ እመቤት ቤተክርስቲያን ጠላቶቿ ገነው፣ ገፊዎቿ በዝተው፣ አቅሟ ተዳክሞ፣ ሰፊ እጇ ሰልሎ (ዝሎ) ታይታለች። ቢሆንም የሲኦል ደጆች እንኳን አይችሏትም። ትናንትንም እንዲህ እያለፈች እዚህ ደርሳለች። እንደሌሎች በእርዳታ እና በበጀት ሌሎችን ለመጫን እና ለማጥቃት የበላይ ለመሆን ሌላ ተልእኮ ይዛ የምትንቀሳቀስ ተቋም አይደለችም።
ትናንት የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል በደመራ በእጣን ጢስ ከተቀበረበት ከቆሻሻው ሥር እንዳላገኘችና እንዳላወጣችው ዛሬ ኢትዮጵያን የተጫናትን መከራ፣ መገፋፋት፣ መከፋፈል፣ መገዳደል፣ ለማስወገድ ደመራውን ደምሮ ጢሱን አጢሶ መስቀሉን ለማክበር ከፍ ከፍ ለማድረግ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብልሹ አሰራር እና ቆሻሻ ተግባር ለጊዜውም ቢሆን የመስቀልን በአል የአገራችን የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች እንቅፋት ሆነዋል።
በሁሉም አቅጣጫ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ እንባውን የሚያነባበት፣ ዋይታና እሮሮ የሚያሰማበት፣ በአላቶቹን በአደባባይ ሳይሆን እንደ ዘመነ ሰማእታት ከምድር በታች እንዲያከብር የሚጠበቅበት እየሆነ መጥቷል።
የመስቀል በአል ያነጋግረን እንጂ የጥምቀተ ባህር ነገርም ከተነሳ እጅን በአፍ ላይ አስጭኖ የሚያስቆዝም ነው።
ለመፍትሔው ብዙ የወጣት ማህበራት፣ ማህበረ ካህናት፣ ቤተክህነት፣ ሲኖዶስ ይንቀሳቀሳል። ነገር ግን ችግሩን ሊቀርፉት አልቻሉም። በቤተክርስቲያን ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ሳቢያ ብዙ የሚደራጁ በአካልና በየሚድያው (ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ) የሚደራጁ ምእመናን ሞልተዋል፤ ይሁን እንጂ ከተሰባሰቡበት አላማ ውጭ የአክቲቭስቶችና የዩቲዩበሮች እንጀራ ከመሆን አልዘለሉም። ይህም የውስጥ ችግራችን የመስቀሉን ሃይል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚጣሉ የቆሻሻ አይነቶች ናቸው።
የመስቀሉን ክብር የሚገልጥ መሪ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። መስቀሉ የአማንያን ብቻ ሳይሆን ላላመኑትም ይጠቅማል። ከመስቀሉ ጋር የተቀበረ ፍትሕ ለኦርቶዶክሳዊያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በእምነት ለማይመስሉን ጩኸታቸው ለታፈነ የእምነት ተቋማትና ምእመናን ሁሉ ፍትህ ያሰጣል። ሽቅብ ወደላይ የሚሸኑትን ግፈኞች አደብ ያስገዛል ለመንግሥት እና የጸጥታ አካላት ሳይቀር የራስ ምታት የሆኑትን ሥርአት ያስይዛል።
በመሥቀል በአል ሥም አገሪቱ ላይ የሚፈጸሙ ሥርአት አልበኝነት የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብቻ መስሎን እንደ ጠላት ተመልክተው ደስታም ተሰምቶዎት ከሆነ ተሳስተዋል።
ይህ የጽንፈኝነት አካሄድ ኢትዮጵያዊ መስሊሙን፣ ፕሮቴስታንቱን፣ ካቶሊኩን፣ የይሖዋ ምሥክሩን፣ ወንጌላውያንን፣ ዋቄፈታውን፣ ባሕሉን፣ ወጉን፣ ታሪክን ሁሉ አንድ በአንድ መንካቱ አይቀሬ ነው። ስለዚህ አብሮ መንቃት አብሮ ቆሻሻውን ቆፍሮ ተራራውን ንዶ መስቀሉን አውጥቶ፣ ክብሩን ገልጦ፣ በአሉን በጋራ ማክበር የተሻለ መፍትሔ ነው።
ሰፊዋን ኦርቶዶክስ ከናቁና ከነቀነቁ ወደሌላው የማይመጡበት ምንም ምክንያት የለም። እነዚህን ሰወች ሃይማኖተኛ አድርጎ ብቻ ማየት፣ የእምነቱ ጥላቻ ብቻ አድርጎ ማየት ትልቅ ስህተት ነው፤ የትኛውም ሃይማኖተኛ በምንም መለኪያ ይህንን የማድረግ ሞራል የለውምና። ይህ ተግባር አገርን የማፍረስ ተልእኮ እንጂ።
መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ይህንን ችግር የአንድ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማየት የለበትም። ምንአልባት ዛሬ ኦርቶዶክስ እና ሙስሊም በእምነቱ ምክንያት ተገድሏል ያልን እንደሆነ የትናንቱን የሌሎች ቤተእምነቶች መቃጠል እና የምእመናን ሞት አንዘንጋ። ነገም የተደገሰልን እልቂትና ውድመት ሊኖር ስለሚችል በአንድነት በመቆም አገርንና ሕዝብን ልንጠብቅ ይገባል።
ችግሩ ዘላቂ ባይሆንም መስቀሉ ከተቀበረበት እስኪወጣ ክልከላዎች እስኪነሱ ቆሻሻውን ከመድፋት ይልቅ ማንሳት ላይ እስካልተረባረብን ድረስ ይቀጥላል።
ስለዚህ አገርንና ቤተክርስቲያንን ለመታደግ መሰባሰባችንን አንተው። ቆሻሻ (ብልሹ አሰራርን፣ ሙስናን፣ ስልጣንን አላግባብ መጠቀምን፣ ዘረኝነትን፣ ተረኝነትን፣ የግል ጥቅም ማስቀደምን) መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ መጣልን እናቁም እንዲህ እያደረግን የምንቀጥል ከሆነ የቤተክርስቲያንን እና የአገርን ትንሳኤ ቀን እናረዝመዋለንና።
ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣት ወራት የፈጀባት ሕዝቡ የጣለው የቆሻሻ ክምር ብዛት ነው። እንዲሁ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መቅረብም ሆነ መራቅ ምክንያቱ እኛ በምናጠራቅመው አይነት እና የቆሻሻ ብዛት ስለሚወሰን ጥንቃቄ እናድርግ።
መስቀሉ የሚወጣበት የመዳን ቀን የሚቀርብበት የሰወች እኩልነት የሚረጋገጥበት ቀን እንዲቃረብ ተራራውን ለመናድ፣ መስቀሉን ለማክበር ቁፋሮውን እንቀላቀል።
በየሙያ መስካችን በየተሰማራንበት ተራራውን እንናድ፤ (ጥላቻ፣ መከፋፈል፣ መጠቃቀም፣ ወዘተ) ይወገድ። ያኔ የመስቀሉም የሆነ የኢትዮጵያ ክብር ይገለጣል። ብዙዎች ይፈወሳሉ። ይድናሉ። ጎባጣው አሰራር ይቀናል፣ ለምጻሙ ይነጻል፣ የሞተ ተስፋችን ይለመልማል፣ እውሩ አመራራችን ይስተካከላል። እንባችን ይታበሳል።
ሕዝብና መንግሥትም በሰላም እጅ ለእጅ ተያይዞ ለልማትና ለሰላም ይሰለፋል። ኢትዮጵያ አገራችን ቁጥር አንድ ታላላቅ አገሮች አንዷ ትሆናለች። ኢትዮጵያውያን የስደት መከራቸው ማብቂያ ያገኛል። አማንያን በሰላም አምልኮአቸውን ያከናውናሉ። ነጋዴ ነግዶ አርሶ አደር አርሶ አርብቶ አደር አርብቶ ሰርቶ አዳሪ ሰርቶ ያልፍለታል። አውርቶ አደር እና አባልቶ/አዋግቶ አደሮች ቦታ ያጣሉ። በነው ከስመው ይጠፋሉ።
መስቀል መከራ ቢሆንም ቅሉ እኒህን ሁሉ የማሸነፍ ሃይል ስላለው ሁሉን ድል አድርጎ በአሉን በሰላም የምናከብርበትን ዘመን ቅርብ ያድርግልን።
በፍጹም መንፈሳዊ ቅናት ፍትሕን እንፈልግ፣ በፍጹም ትሕትና መፍትሔ ለማግኘት እንምከር። ከንግሥት እሌኒ የምንማረው በትህትና ወደ አባቶች ለምክር መቅረብን፣ በመንፈሳዊ ቅናት ለአግልግሎት መሯሯጥን፣ ለአገር ከፍታ ከክብር ዝቅ ማለትን ነውና። ዝቅ ብለን አገርን ከፍ እናድርጋት።
ከአጥብያ ቤተክርስቲያን እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅበትን ያድርግ እያደረገም ይገኛልና እኛም የበኩላችንን እንወጣ።
በጾም፣ በጸሎት፣ በምሕላ፣ በሱባኤ፣ በንሰሐ፣ እግዚአብሔርን ምላሽ ልንጠይቅ መንግሥትንም በመደራጀት በሥርአት እና ሕጉን ተከትሎ በመንፈሳዊ ሥነምግባር መብታችንን ልንጠይቅ ይገባል።
የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሆይ የጥፋት ጭለማ ውጦናልና ወዴት አለህ? በሚያጠፉን ጠላቶቻችን ተከበናልና ወዴት አለህ? ገጸ ምሕረትህ ወደኛ ትመለስ።
መስቀል ለእኛ ለምናምን ሃይላችን ነው፣ መድኋኒታችን ነው፣ የክብራችን መገለጫ ነው።
እውነት እንዳይደበቅ አጋሩት።
ይቆየን።
በቴሌግሬም ገጽ ለመከታተል
@deressereta