ዓርብ 15 ማርች 2013

የመወለድ ሳምንት! እስከ መጋቢት 22 2013



የመወለድ ሳምንት!     እስከ መጋቢት 22 2013



ወደ ኋላ ረጅም ዓመት ስንመለስ ግጥም እጽፍ እንደ ነበረ ትዝ ይለኛል!
እንዲሁ ደሞ ከረጅም ዓመት በኋላ እንዴት እንዳቆምኩት በማይታወቅ ሁናቴ አቁሜ እራሴን አገኘሁት! ካለመፃፍ መፃፍ ቢሻልም የኔ ግን እንኳንም ቀረ ሽ ሽ ሽ ት ት ት ይበዛዋልና (በሳድስ ነዉ የሚያልቁት ማለቴ ነዉ) ከሳድስ ጋር የተቆራኘ ነገር ኖሮኝ ሳይሆን ለግጥም ሳድሶች ቤት ለመምታት ቀለል ስለሚሉ እንጂ፤ አሁንም የግጥም ዛሬ (ዛር) ሳይሆን ቅዠቴ ሲነሳብኝ ከዚያ የተሻለ አልፅፍም ጥሎብኝ ግን እንደ ግጥም ነፍሴን የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ማንበብ እወዳለሁ ጊዜዉ አለፈብኝ እንጂ ገጣሚ ሳላፈቅር እቀራለሁ ብላችሁ ነዉ? (ሳቁልኝ ወይም ሳቁብኝ ጎበዝ ይህንን በግጥም ፍቅር እብደቴን) .. … …
ከዚያ በኋላ እንዲሁ የግጥም ፍቅሬ ወረት ሆነና ስሙን ጠንቅቄ ወደማላቀዉ ( ጓደኞቼ ሥነ-ፅሁፍ ወደሚሉት) አዘነበልኩ፤ የሆነ ጊዜ ወደ 1992 ዓ.ም. አካባቢ ይመስለኛል ባልንጀራዬ፣ በጣም የምወዳት እህቴ እና ባለዉለታዬ (መምህር አፀደ ማርያም ስሻዉ በአሁኑ ሰዓት ኮኮበ ፅባህ ት/ቤት በማስተማር ላይ ትገኛለች)(እባካችሁ አመስግኑልኝ) እባክህ ፃፍ ፃፍ ስትለኝ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ መፃህፍትን ስትገዛልኝ፣ ስታበረታኝ … … …. ለዚህ በቅቼላት ድፍን አንድ ዓመት ሞላኝ የሚገርመዉ ግን ዛሬ ድረስ ምን እያረኩ እንደሆንኩ አለማወቋ ነዉ፤ መቸስ ለምስጋና ከተነሳሁ አይቀር እንዲሁ ቁጭ ብዬ ስቧጭር የነበሩትን ነገሮች እስኪ ላንብብልህ እያልኩት የማስቸግረዉንና የግድ በሚያሰኝ መልኩ እንዲህ እንድፅፍ አለበለዝያ ለመፅሔት እና ጋዜጣ አዘጋጆች እንድልክ (ለማናቸዉም አላኩትም እንጂ) ይጎተጉተኝ የነበረዉን ወንድሜ መታገስን፣ በኮምፒዉተር ፅሁፎቼን ትፅፍ የነበረችዉን ወ/ት ፅዮን ፍቅሩን፣ ከምንም በላይ በቃላት ገልጬ የማልጨርሳቸዉን ድርጊቶች በማድረግ በመራዳት ያልተለየችኝን እቴነሽ እጅጉን፣ዉድ ጊዜአቸዉን እንደ መስዋዕት በግ የሰዉልኝ ቤተሰቦቼንና በቃላት ያልጠቀስኳቸዉና በልቤ ዘወትር ያላችሁትን ምስጋናዬ በእግዚአብሔር ሰፊ እጅ ይሰጣችሁ፡፡ከምንም በላይ ደግሞ Ethiopia,USA,Germany,Russia,Switzerland,Sweden,Israel,Italy,Unite Kingdom,France,… በመሆን ወርቅ የሆነ ጊዜአችሁን በመሰዋት ስታነቡ የነበራችሁትን ከመቀመጫዬ ተነስቼ እጅ እነሳለሁ፡፡
ቀጠል አድርጌ ሳክልም ስጀምርም ስጨርስም ሁሌ የማመሰግነዉ አምላኬ በመካከል እጅግ ተስፋ የሚያስቆሩረጡ ሂደቶችን እንዳልፍ ብርታቱን ስለሰጠኝ ዛሬ እንደደረስኩ ልነግራችሁ ወዳለሁ፡፡ ይህ እንደ መፃፍ ባይቆጠርም መቸስ እንኳን ረዘም ያለ ነገር ደብዳቤም መፃፍ ይከብድ እንደነበር አዉቅ ስለነበር ብርታት ስለሆነኝ አምላኬ ምስጋና ያስፈልገዋል፡፡ መቼ ይህ ብቻ ፡-

በቂ መረጃ ሳጣ፣
የማፅፍበትን ገንዘብ ሳጣ፣
የሚፅፍልኝ ሰዉ ሲቸግረኝ፣
ሙያዊ የምክር አገልግሎት የሚሰጠኝ የሰዉ ያለህ ስል፣
የፃፍኩትን አንባቢ ሲጠፋ፣
የምፅፈዉ ጉዳይ ኖሮኝ ጊዜ ስቸገር ፤ …
አምላኬ ሁሉ ቦታ የክብር ስፖንሰርና አጋር በመሆን ከአጠገቤ ስለነበር ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

ድካሜንስ ለምን አልናገርም፡-

የጀመርኩትን ቀኑን ጠብቄ አለማዉጣት፣
ይቀጥላል እያልኩ በዚያዉ መጥፋት፣
ያልበሰሉ ፅሆፎችን መልቀቅ፣
አስፈላጊ መረጃዎችን በጊዜዉ አለማድረስ፣… እነዚህ ሁሉ እኔ የማዉቃቸዉ ሲሆኑ እናንተ የምታዉቁት እጅግ ከዚህ ይበዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡በቀጣዩ ዘመናችን አብረን ስለምንዘልቅ፣ ስለምንሰራ፣ ይህ መጦመሪያ የሁላችንም እንደመሆኑ መጠን ጥሩ ነገር አብረን እንደምንሰራ ተስፋ አለኝ፡፡
ይህንን ጦማር የጀመርኩት በፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር መጋቢት 22 2012 ነበር ይህ ሳምንት የዚህን ጦማር መወለድ እያሰብን አስተያየቶችን በመስጠት፣ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ ያመለጡንን ወደ ኋላ እየተመለስን በማንበብ፣ … የምናከብርበት ሳምንት ነዉ፡፡ክቡራን አንባቢዎቼ አሁንም እንኳን ለጦማራችን አንደኛ ዓመት አደረሰን፡፡



ሰኞ 11 ማርች 2013

እናት


እናቴ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ
ከጎኔኮ ሳጣሽ ይባክናል ዐይኔ
ዛሬ ዛሬ የነ ሻኪራ፡ የነ ቢዮንሴ፡ ቱፓክ፡ሮናልዶ፡ ሜሲ፡ … እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ፎቶ ገበያዉንና ቤታችንን ከማጨናነቁ በፊት፡ ከከተማዉም አልፎ ገጠሩ ድረስ ዘልቆ ከመግፋቱ በፊት… ከላይ እንደ ቀልድ የጠቀስናት ጥቅስ የቤት ማድመቅያ፡የመልዕክት ማስተላለፍያ፡ እናቱ ወንዝ የወረደችበትም፡ እናቱ የሞተችበትም በሃያ አምስት ሳንቲም ከጎዳና ላይ እየገዛ ያለዉ በእስቴፕለር፡ የሌለዉ በእሾክ ወይ በሚስማር ከጠፋም በሙቅ ይለጥፋታል፤ ዛሬ ግን ግጥምም የለ፡የምትሞትም እናት የለች (በወሊድ ምክንያት አንድም እናት መሞት የለባትምና፤አንድም እናቶች ቆመዉ ልጆች ፍግም እያሉ/እየተቀጩ/ ነዉና)፡ ሚስማርም፡ እሾክም፡ ኧረ ሙቅም እንዃን ለወረቀት መለጠፍያ ለወገብ መጠገኛም የለም፡፡
ዛሬ ከመኖርያ ቤታችን ይልቅ የእናት ነገር በፌስ ቡክ ገፅ ላይ እየተለቀቀ LIKE በማድረግ ተቀይሯል፤ በየቢል ቦርዱ መሰቀል የስራ እድልም ሆኗል (ለማስታወቅያ ባለሙያዎች) ፡ ስለ እናት ከተነሳ ብዙ ግጥም መግጠም፡ ብዙ መቀኘት፡ ብዙ ማዜም ይቻላል፡፡ነገር ግን ያልተቻለዉ ሞቷን ማስቀረትና የሚደርስባትን ግፍ፡ መከራ፡ስድብ፡የጉልበት ብዝበዛ፡ … ናቸዉ፡፡ የፌስቡክ ገፅ ላይ የእናት ዉለታ ተዘርዝሮ ተዘርዝሮ ከዛ እናታችሁን የምትወዱ እስኪ LIKE አድርጉ ሲባል እኔን ጨምሮ አናልፈዉም LIKE እናደርጋለን፤ በጣም ጥሩ ነገር ነዉ እንዲህ የእናትን ነገር በአደባባይ LIKE ማድረግ፡ በሰላማዊ ሰልፍ መግለጥ፡ ቢል ቦርድ መስቀል፡የእናቶች ቀን ብሎ ማክበር፡ የተለያዩ ፎረሞችን  ማዘጋጀት፡የተለያዩ ተቋማትን በስሟ ማቋቋም፡ … ወዘተ በጣም ደስ ይላል፡፡ ቀዳሚዉ ተደሳች እኔ ነኝ ማጋነን ካልሆነብኝ አለበለዝያም የእኔን ፍቅር አስበልጬ የእናንተን በማሳነስ ቅር ካላሰኘኋችሁ፤ነገሩ ወዲህ ነዉ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አለ ያገሬ ሰዉ፡ ላም ባልዋለበት ኩበት እየተለቀመ ሆኖ ነዉ እንጂ እንደዉ ማን ይሙት እቤት ተቀመወጠን ፌስቡክ ገፃችንን ከፍተን CHAT እያደረግን እናታችን (ሚስት፡ እህት፡ልጅ)ብትልከን መታዘዙን እምቢ የምንል ልጆች ስለ እናት POST የተደረገዉን አይተን LIKE የምናደርግ ፌስቡከሮች የፌስቡክ እናት ለብቻ አለንዴ? LIKE የምናደርጋት ጥያቄ አለኝ፡፡እቤት ያለችዋን አስጠልቶ የፌስቡዃን የሚያስወድደን?መታዘዝ አቅቶን ፍቅር ማን አስተምሮን ነዉ LIKE የምናደርገዉ? ወይንስ የLIKE ትርጉሙ አልገባን ይሆን እንዴ፤ ማን ያዉቃል እንደ ምርጫ ድምፅ ካርድ እያጭበረበርን ይሆናል፡፡ አንድ እዉነት ልንገራችሁ LIKE በማድረግ የእናት ዉለታና ፍቅር አይገለጥም ሌላዉ ቢቀር ጡቶቿን እያጠባች ስታሳድገን ጡትን በፎቶግራፍ ወይም ጎንበስ ብላ በማየት እንደኛ LIKE አድርጋ፡ ወይም ማጥባት ነበር እያለች አይደልም ያሳደገችን፡፡ልጆች ምናልባት ዛሬ የተፈጠሩ ጡታችን ይበላሻል በማለት ልጆቻቸዉን ጡት የማያጠቡ ከሺ አንድ በማየት የእናትን ፍቅርና ዉለታ LIKE በማድረግ ብቻ የሚጠናቀቅ እንዳይመስለን፡፡በተለይ ወጣቶች ዛሬ በጉርምስና ወቅት እናቶች የሚሉን ነገር እንደ ሬት የሚመረን ከፍ ሲል የሚናፍቅና የሚጥም መሆኑን እናት አንዴ ካለፈች (መናገር ካቆመች ወድያ)እንደማይገኝና እንደማይገኝ እኔ ልንገራችሁ፤የደረሰበት ያዉቃልና፡፡
እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
ቅማል ታወጣለች በጨለማ ዳብሳ
የተባለዉ ግጥሙ ቤት ስለሚመታ ተብሎ አይደለም፤ አልያም ስለሚያምር ተብሎ የተሰካካ ቃላት አይደለም፤እዉነትና ህይወት ስለሆነ እንጂ፡፡የቀን ድካም አልበቃ ብሏት ሌትም ፍቅሯን ፀጉር በመዳበስ ትገልጣለች፤ፍቅሩ ያልገባችዉ ምስጢሩ ያልተገለጠላችሁና እናት ያላችሁ እናቶቻችሁን አደራ! በክፉ ቀን እናትችሁን ለሰሪዉ እንደኔ ያስረከባችሁ ሚስታችሁን፡ እህቶቻችሁን፡ልጆቻችሁን ተናከባከቡ፡፡እናት ምንም እንዃን በቃላት መገለጥ ባትችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታ ዓለምን ለማዳን ባሰበ ጊዜ ቅድመ ዓለም( የሰዉ ልጅ ከመፈጠሩ በፊት) በህሊና አምላክ ታስባ ትኖር እንደነበር ሁሉ ሴት ልጅም ስትፈጠር እናት በመሆን ስትታሰብ የምትኖር ናትና ሴት ልጅን እንንከባከባት፡ቅድሚያ እንስጣት፡ዝም ብለን LIKE በማድረግ ማለፍ፡ በየአደባባዩ መጮህ፡የሚሰቀልና የሚለጠፍ ነገር መስቀልና መለጣጠፍ ብቻ ሳይሆን፡ የሚደርስባትን ጥቃት እንከላከል፡ ፍትህ አናጓድልባት፡ፆታዊ ጥቃት፡የወሲብ ትንኮሳን እንዋጋላት፤በቤት ዉስጥም በአደባባይም ፍቅራችንን እንግለጥላት፡፡
ምናልባት ሁላችንም የእናትን ሞት አንወድ ይሆናል የዛኑ ያህል ደግሞ እናትነት (እናት መሆን) አይገባንም፤ሥለሔዋን ስህተት እንጂ ስለሔዋን እናትነት የዘነጋን ይመስለኛል፡፡ ያለቦታዉ አንስቼ እንዳልዘባርቅ እንጂ ሔዋን የተሳሳተችዉና ያሳሳተችዉ በማን ባህሪ በማን አጥንት በማንስ ስጋና ደም ነዉ? ተከድኖ ይብሰል አንልም እግዚአብሔር ቢፈቅድ አንድ ቀን አንስተን እናፍረጠርጠዋለን ዓለም የጠፋዉ በአዳም ደካማ ባህሪ መሆኑን፡፡
እናት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀኗ ተሸክማ የበላችዉን አብልታ የጠጣችዉን አጋርታ ሙቀት ሰጥታ በጣርና በጋር በምጥ በህመም ወልዳ እንደገናም ከእናት ጡት ሌላ ምግብ መመገብ እስኪጀምር ድረስ ጡት አጥብታ በማሳደግ ሂደት ዉስጥ አዝላ፡አቅፋ፡ የሽንት ጨርቅ አጥባ፡ ምግቡን አብስላ፡ቋንቋ እስኪለምድ በእናትና ልጅ ቋንቋ ብቻዋን ተግባብታ፡በማሳደግ እድሜዉ ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ ይለያታል፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሁሉ ሸክም የእናት ብቻና ብቻ ነዉ፤ ከዚህ ሁሉ ዉጣ ዉረድ በኋላም እንደ አጋጣሚም ሆነ በተለያየ ምክንያት ልጅ ባህሪዉ ቢከፋ ለወቀሳ (ልጅሽ እንዲህ አድርጎ በማለት)ጣት ይቀሰርባታል፡ብቻዋን ወደዚህ ዓለም በፈቃድዋ ያመጣችዉ ይመስል፡፡መቼ ይህ ብቻ ልጆችም ነፍስ ሲያቁ እናቶቻቸዉን በቤት ትተዉ ከኣባታቸዉ ጋር በአደባባይ መታየት የሚያሰደስታቸዉ ልጆች ሞልተዋል፡፡ይህም ግድ የለም ሴት ሆነዉም እንዲህ በመሆን የወለደችን ያሳደገችን እናት የሚሳደቡ ሴቶች ሞልተዋል፡፡የሴትነትን ክብር የሚያጎድፉም ሴቶች ተበራክተዋል፤ ነገር ግን LIKE ከማድረግ እጃቸዉ አይቦዝንም፡፡
የእናት ፍቅር እንዲህ ተብሎ አይዘለቅም እያደር እየዋለና እያደረ እየጣመና እየጣፈጠ የሚሄድ ልዩ ስጦታ ነዉ፤አንዳንዶቻችን ብቻ ሳይሆን አብዛኞቻችን እንዳጋጠመን እናት ከእናትነቷ ባሻገር የቅርብ ጓደኛ፡ አማካሪ፡ወንድም፡እህት … ወዘተ የሆነችዋ ደግሞ ስታልፍ ፀፀቱ የእግር እሳት ይሆንብናል ባዶ እንሆናለን፡፡ሁል ጊዜ ባዶ ነን! ብቸኛ ነን! ምንም ነን!
ከእናት አልባነት ቤተሰብ አልባ እንሆናለን የቤቱ ማገር፡ዋልታ፡ መሰርት፡….የለችምና፤በአንድነት እህትም፡ጓደኛም፡አማካሪዋም፡… ተነቅላ ቀዬዉን ጥላ ሄዳለችና፡፡ታድያ ይህች እናት ለምን ትሙት?ይህች እናት ለምን መከራና ስቃይ ይድረስባት?በወሊድ ሰዓት ለምን ትሰቃይ?... እንዴት አትችልም ተብላ ትናቅ?
እናቴ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ
ከጎኔኮ ሳጣሽ ይባክናል ዐይኔ
በምድር ያጣሁሽ እናቴ በሰማይ መልካም እረፍት ይሁንልሽ!ሁሌም ወድሻሁ!ክብር ለእናቶች! ክብር ለሴቶች!

ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...