ሰኞ 11 ማርች 2013

እናት


እናቴ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ
ከጎኔኮ ሳጣሽ ይባክናል ዐይኔ
ዛሬ ዛሬ የነ ሻኪራ፡ የነ ቢዮንሴ፡ ቱፓክ፡ሮናልዶ፡ ሜሲ፡ … እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች ፎቶ ገበያዉንና ቤታችንን ከማጨናነቁ በፊት፡ ከከተማዉም አልፎ ገጠሩ ድረስ ዘልቆ ከመግፋቱ በፊት… ከላይ እንደ ቀልድ የጠቀስናት ጥቅስ የቤት ማድመቅያ፡የመልዕክት ማስተላለፍያ፡ እናቱ ወንዝ የወረደችበትም፡ እናቱ የሞተችበትም በሃያ አምስት ሳንቲም ከጎዳና ላይ እየገዛ ያለዉ በእስቴፕለር፡ የሌለዉ በእሾክ ወይ በሚስማር ከጠፋም በሙቅ ይለጥፋታል፤ ዛሬ ግን ግጥምም የለ፡የምትሞትም እናት የለች (በወሊድ ምክንያት አንድም እናት መሞት የለባትምና፤አንድም እናቶች ቆመዉ ልጆች ፍግም እያሉ/እየተቀጩ/ ነዉና)፡ ሚስማርም፡ እሾክም፡ ኧረ ሙቅም እንዃን ለወረቀት መለጠፍያ ለወገብ መጠገኛም የለም፡፡
ዛሬ ከመኖርያ ቤታችን ይልቅ የእናት ነገር በፌስ ቡክ ገፅ ላይ እየተለቀቀ LIKE በማድረግ ተቀይሯል፤ በየቢል ቦርዱ መሰቀል የስራ እድልም ሆኗል (ለማስታወቅያ ባለሙያዎች) ፡ ስለ እናት ከተነሳ ብዙ ግጥም መግጠም፡ ብዙ መቀኘት፡ ብዙ ማዜም ይቻላል፡፡ነገር ግን ያልተቻለዉ ሞቷን ማስቀረትና የሚደርስባትን ግፍ፡ መከራ፡ስድብ፡የጉልበት ብዝበዛ፡ … ናቸዉ፡፡ የፌስቡክ ገፅ ላይ የእናት ዉለታ ተዘርዝሮ ተዘርዝሮ ከዛ እናታችሁን የምትወዱ እስኪ LIKE አድርጉ ሲባል እኔን ጨምሮ አናልፈዉም LIKE እናደርጋለን፤ በጣም ጥሩ ነገር ነዉ እንዲህ የእናትን ነገር በአደባባይ LIKE ማድረግ፡ በሰላማዊ ሰልፍ መግለጥ፡ ቢል ቦርድ መስቀል፡የእናቶች ቀን ብሎ ማክበር፡ የተለያዩ ፎረሞችን  ማዘጋጀት፡የተለያዩ ተቋማትን በስሟ ማቋቋም፡ … ወዘተ በጣም ደስ ይላል፡፡ ቀዳሚዉ ተደሳች እኔ ነኝ ማጋነን ካልሆነብኝ አለበለዝያም የእኔን ፍቅር አስበልጬ የእናንተን በማሳነስ ቅር ካላሰኘኋችሁ፤ነገሩ ወዲህ ነዉ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አለ ያገሬ ሰዉ፡ ላም ባልዋለበት ኩበት እየተለቀመ ሆኖ ነዉ እንጂ እንደዉ ማን ይሙት እቤት ተቀመወጠን ፌስቡክ ገፃችንን ከፍተን CHAT እያደረግን እናታችን (ሚስት፡ እህት፡ልጅ)ብትልከን መታዘዙን እምቢ የምንል ልጆች ስለ እናት POST የተደረገዉን አይተን LIKE የምናደርግ ፌስቡከሮች የፌስቡክ እናት ለብቻ አለንዴ? LIKE የምናደርጋት ጥያቄ አለኝ፡፡እቤት ያለችዋን አስጠልቶ የፌስቡዃን የሚያስወድደን?መታዘዝ አቅቶን ፍቅር ማን አስተምሮን ነዉ LIKE የምናደርገዉ? ወይንስ የLIKE ትርጉሙ አልገባን ይሆን እንዴ፤ ማን ያዉቃል እንደ ምርጫ ድምፅ ካርድ እያጭበረበርን ይሆናል፡፡ አንድ እዉነት ልንገራችሁ LIKE በማድረግ የእናት ዉለታና ፍቅር አይገለጥም ሌላዉ ቢቀር ጡቶቿን እያጠባች ስታሳድገን ጡትን በፎቶግራፍ ወይም ጎንበስ ብላ በማየት እንደኛ LIKE አድርጋ፡ ወይም ማጥባት ነበር እያለች አይደልም ያሳደገችን፡፡ልጆች ምናልባት ዛሬ የተፈጠሩ ጡታችን ይበላሻል በማለት ልጆቻቸዉን ጡት የማያጠቡ ከሺ አንድ በማየት የእናትን ፍቅርና ዉለታ LIKE በማድረግ ብቻ የሚጠናቀቅ እንዳይመስለን፡፡በተለይ ወጣቶች ዛሬ በጉርምስና ወቅት እናቶች የሚሉን ነገር እንደ ሬት የሚመረን ከፍ ሲል የሚናፍቅና የሚጥም መሆኑን እናት አንዴ ካለፈች (መናገር ካቆመች ወድያ)እንደማይገኝና እንደማይገኝ እኔ ልንገራችሁ፤የደረሰበት ያዉቃልና፡፡
እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ
ቅማል ታወጣለች በጨለማ ዳብሳ
የተባለዉ ግጥሙ ቤት ስለሚመታ ተብሎ አይደለም፤ አልያም ስለሚያምር ተብሎ የተሰካካ ቃላት አይደለም፤እዉነትና ህይወት ስለሆነ እንጂ፡፡የቀን ድካም አልበቃ ብሏት ሌትም ፍቅሯን ፀጉር በመዳበስ ትገልጣለች፤ፍቅሩ ያልገባችዉ ምስጢሩ ያልተገለጠላችሁና እናት ያላችሁ እናቶቻችሁን አደራ! በክፉ ቀን እናትችሁን ለሰሪዉ እንደኔ ያስረከባችሁ ሚስታችሁን፡ እህቶቻችሁን፡ልጆቻችሁን ተናከባከቡ፡፡እናት ምንም እንዃን በቃላት መገለጥ ባትችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታ ዓለምን ለማዳን ባሰበ ጊዜ ቅድመ ዓለም( የሰዉ ልጅ ከመፈጠሩ በፊት) በህሊና አምላክ ታስባ ትኖር እንደነበር ሁሉ ሴት ልጅም ስትፈጠር እናት በመሆን ስትታሰብ የምትኖር ናትና ሴት ልጅን እንንከባከባት፡ቅድሚያ እንስጣት፡ዝም ብለን LIKE በማድረግ ማለፍ፡ በየአደባባዩ መጮህ፡የሚሰቀልና የሚለጠፍ ነገር መስቀልና መለጣጠፍ ብቻ ሳይሆን፡ የሚደርስባትን ጥቃት እንከላከል፡ ፍትህ አናጓድልባት፡ፆታዊ ጥቃት፡የወሲብ ትንኮሳን እንዋጋላት፤በቤት ዉስጥም በአደባባይም ፍቅራችንን እንግለጥላት፡፡
ምናልባት ሁላችንም የእናትን ሞት አንወድ ይሆናል የዛኑ ያህል ደግሞ እናትነት (እናት መሆን) አይገባንም፤ሥለሔዋን ስህተት እንጂ ስለሔዋን እናትነት የዘነጋን ይመስለኛል፡፡ ያለቦታዉ አንስቼ እንዳልዘባርቅ እንጂ ሔዋን የተሳሳተችዉና ያሳሳተችዉ በማን ባህሪ በማን አጥንት በማንስ ስጋና ደም ነዉ? ተከድኖ ይብሰል አንልም እግዚአብሔር ቢፈቅድ አንድ ቀን አንስተን እናፍረጠርጠዋለን ዓለም የጠፋዉ በአዳም ደካማ ባህሪ መሆኑን፡፡
እናት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህፀኗ ተሸክማ የበላችዉን አብልታ የጠጣችዉን አጋርታ ሙቀት ሰጥታ በጣርና በጋር በምጥ በህመም ወልዳ እንደገናም ከእናት ጡት ሌላ ምግብ መመገብ እስኪጀምር ድረስ ጡት አጥብታ በማሳደግ ሂደት ዉስጥ አዝላ፡አቅፋ፡ የሽንት ጨርቅ አጥባ፡ ምግቡን አብስላ፡ቋንቋ እስኪለምድ በእናትና ልጅ ቋንቋ ብቻዋን ተግባብታ፡በማሳደግ እድሜዉ ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ ይለያታል፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሁሉ ሸክም የእናት ብቻና ብቻ ነዉ፤ ከዚህ ሁሉ ዉጣ ዉረድ በኋላም እንደ አጋጣሚም ሆነ በተለያየ ምክንያት ልጅ ባህሪዉ ቢከፋ ለወቀሳ (ልጅሽ እንዲህ አድርጎ በማለት)ጣት ይቀሰርባታል፡ብቻዋን ወደዚህ ዓለም በፈቃድዋ ያመጣችዉ ይመስል፡፡መቼ ይህ ብቻ ልጆችም ነፍስ ሲያቁ እናቶቻቸዉን በቤት ትተዉ ከኣባታቸዉ ጋር በአደባባይ መታየት የሚያሰደስታቸዉ ልጆች ሞልተዋል፡፡ይህም ግድ የለም ሴት ሆነዉም እንዲህ በመሆን የወለደችን ያሳደገችን እናት የሚሳደቡ ሴቶች ሞልተዋል፡፡የሴትነትን ክብር የሚያጎድፉም ሴቶች ተበራክተዋል፤ ነገር ግን LIKE ከማድረግ እጃቸዉ አይቦዝንም፡፡
የእናት ፍቅር እንዲህ ተብሎ አይዘለቅም እያደር እየዋለና እያደረ እየጣመና እየጣፈጠ የሚሄድ ልዩ ስጦታ ነዉ፤አንዳንዶቻችን ብቻ ሳይሆን አብዛኞቻችን እንዳጋጠመን እናት ከእናትነቷ ባሻገር የቅርብ ጓደኛ፡ አማካሪ፡ወንድም፡እህት … ወዘተ የሆነችዋ ደግሞ ስታልፍ ፀፀቱ የእግር እሳት ይሆንብናል ባዶ እንሆናለን፡፡ሁል ጊዜ ባዶ ነን! ብቸኛ ነን! ምንም ነን!
ከእናት አልባነት ቤተሰብ አልባ እንሆናለን የቤቱ ማገር፡ዋልታ፡ መሰርት፡….የለችምና፤በአንድነት እህትም፡ጓደኛም፡አማካሪዋም፡… ተነቅላ ቀዬዉን ጥላ ሄዳለችና፡፡ታድያ ይህች እናት ለምን ትሙት?ይህች እናት ለምን መከራና ስቃይ ይድረስባት?በወሊድ ሰዓት ለምን ትሰቃይ?... እንዴት አትችልም ተብላ ትናቅ?
እናቴ አትሙቺ ልሙትልሽ እኔ
ከጎኔኮ ሳጣሽ ይባክናል ዐይኔ
በምድር ያጣሁሽ እናቴ በሰማይ መልካም እረፍት ይሁንልሽ!ሁሌም ወድሻሁ!ክብር ለእናቶች! ክብር ለሴቶች!

ሐሙስ 14 ፌብሩዋሪ 2013

ቅዱስ ቫላንታይን


ቅዱስ ቫላንታይን
በየአመቱ በፈረንጆች feb 14 ቀን በአሜሪካና በቀሪዉ ክፍለ ዓለማት የተለያዩ አበባዎችን፣ ሻማዎችን፣ ስጦታዎችን፣ ፍቅረኛሞች በመለዋወጥ ቅዱስ  ቫላንታይንን በማሰብ ያሳልፋሉ፡፡በአገራችንም ብዙ ወጣቶች በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል፡፡በዓልን ማክበር ምንም የከፋ ነገር ባይኖረዉም ለምን እናከብራለን ? ፋይዳዉ ምንድን ነዉ? የምታከብረዉ አገር የበዓሉ መከበር ዜጋዋን ምን ጥቅም ይሰጠዋል? የሚሉት ነገሮች ሊነሱ ይገባቸዋል፡፡
ዛሬ ወጣቱ የቄስ ቫላንታይንን ቀን እያከበረ ባለበት ሰዓት የበዓሉን ድምቀት እንዳላደበዝዘዉ ብፈራም ወደፈት ግን በአገራችን የሚከበሩትን መጤ በዓላት እናዳስሳለን፤በጎ ጎናቸዉንና መጠፎ ጎናቸዉን እናያለን፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የኮራ የደራ የደመቀ እጅግ በጣም ብዙ በዓላት ሲኖሯት ገሚሶቹ እንዲሁ እንደቫላንታይን ቀን መጤዎች ናቸዉ፡፡ የመጤ በዓላት የአገራችንን ባህል ቅይጥ እንዲሆኑና የባለቤትነት መብት ላይ አጨቃጫቂ ሆነዋል፡፡ የ3000 ዘመን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በንግስተ ሳባ በኩል ከኢየሩሳሌም ያመጣቻቸዉ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ስልጣኔ … ወዘተ ጠቀሜታም ጉዳትም ሲኖረዉ ንግስተ ሳባ ከንጉስ ሰሎሞን ጋር ያላት ግንኙነት እዉን ንግስተ ሳባ ኦትዮጵያዊ ነች ወይ? የሚል ጥያቄን አስነስቷል፤እንኳንስ የመጡት ባህሎችና በዓላት ይቅርና ማለት ነዉ፡፡
ከዚህ ጊዜ አንስቶ (እስራኤላዉያን የንጉስ ሰሎሞንን ልጅ ምኒልክን ተከትለዉ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጊዜ አንስቶ) ዛሬ በብዙ ድካም ልንከላከለዉና ልናስቀረዉ የምንለፋዉ ብዙ በጀት የምንመድብበት የግርዛት ጣጣ አስቀድሞ የኛ አልነበረም፡፡ እንዲሁ በየግል ት/ቤትና በየመንግስት ት/ቤቶች ይልቁንም በየዩኒቨርችቲዎች ሳይቀር የሚከበሩት የከለር ቀን፡የእብደት ቀን ፡የከረባት ቀን፡ … ወዘተ ከባዕዳን አገራት ያመጣናቸዉ በዓላት ናቸዉ::
የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት ወደ መጤ ባህሎች ተቀባይነት ተቀይሮ ዛሬ እነኝህንና ሎሎችን ባህሎች በዓላት በቀላሉ ተቀባይ ለመሆን መቻሉ ዛሬ በዓለም ላይ አነጋጋሪ እየሆነ የመጣዉን በሃይማኖትም ሆነ በባህል የተወገዘዉን የሌዝብያን (የሴት ለሴት መዳራትና መጋባት)፤ የጌዎች (የወንዶች ለወንዶች መዳራትና መጋባት) ሰዶማዊ ግብር በአገራችን ከ14000 በላይ አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ እንዲበቃ ያደረገን ደግሞ ከልካይ ማጣታችንና ባለን ያለመርካት  ክፋና ደጉን ለመለየት የአዕምሮ ብስለት ማጣት ሳይሆን አዕምሮዎቻችንን በአግባቡ ያለመጠቀም አባዜ ነዉ፡፡
ትናንት ለእድገት ፀር ሆነ፡ ወደ ኋላ አስቀረን ልማትን አደናቀፈ እየተባለ ሲወቅስ የነበረዉ የኢ/ኦ/ተዋህዶ ቤተክርስትያን እግዚአብሔርንና ቅዱሳኗን የምታስብበትንና ለምዕመናኗ በረከትን የምታሰጥበት (ዓለም የሰማዕታት ቀን ብላ እንድታከብር ማለት ነዉ) ክብረ በዓላት በአንድ ልደታ፡ በሶስት በዓታ ፡ በአምስት አቦ፡ በሰባት ስላሴ፡ … እያለች ህዝቡን አሳነፈች ተብላ ቅድስት ቤተክርስትያኗ ያለሃጢያቷ ስትብጠለጠል ነበር፡፡አገርንም ሆነ ህብረተሰብን የሚጎዳ ነገር አልነበራትም፤ አክብሩ ብላም አላስገደደችም፡፡ ነገር ግን ት/ቤቶች እየተዘጉ ፣የትምህርት ሰዓት እየተቋረጠ፣ ወጣቱ ወዳልተፈለገ ስነ-ምግባርና የህይወት አቅጣጫ ሲያዘነብል ፣አንድም ሰዉ ሊያወግዝ አለመነሳቱ የሚያስተዛዝብና ቀጣይ ዕጣ ፈንታችን ስጋት ላይ የወደቀ ጉዳይ እንደሆነ ያመላክታል፡፡
በእያንዳንዱ መጤ በዓላት ቀን ወጣቶች በተለያየ ስፍራ አልባሌ በሆነ ሁኔታ ጊዜአቸዉንና ህይወታቸዉን በከንቱ ማባከን እየተለመደ መጥቷል፤ በነዚህ በዓለት አማካይነት ወጣቶች ለመጠጥ ቤት፡ለጭፈራ ቤት፡ ለሽሻ እና ለሲጋራ ማጤሻ፡ ለጫትመቃምና ለተለያዩ ሱሶች መጋለጥ፡ አልፎ ተርፎም ለወሲብ ጥቃት(ለፆታዊ ትንኮሳ)መጋለጥ አብይ መንገድ እየሆነ ይገኛል፡፡እነዚህ አላስፈላጊ ባህሎች፡ በዓላት፡ ቀናት … ጥቅማቸዉንና ጉዳታቸዉን በመለየት ትዉልዱን ለማስተማርና ለመቅረፅ የራሳቸዉን ባህሎች ሊያዳብሩና ሊኮሩበት እንዲችሉ ለማስቻል ወላጆች፡ የሚመለከታቸዉ መንግስታዊ፡ ሃይማኖታዊ፡ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፡ ሚድያዎች … ወዘተ ጠንከር ያለሥራ ሊሰሩ ይገባል፡፡ ዝምታ ወርቅ የማይሆንበትም ጊዜ አለና ዝም አንበል! በተለይ FM ሬድዮኖቻችን ልብ ሊሉትና አገራዊ ግዴታቸዉንና የሚድያ ስነ ምግባሩን ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል፡፡    
በዛሬዉ ዕለት ሱቆች የቀይ አልባሳት መሸጫ፣ የአበባ መሻጫዎች የአበባ ንግዳቸዉ የሚጧጧፍበት፣የስጦታ መሸጫዎችም እንዲሁ ገበያቸዉ የሚደራበት፣የጥበብ ባለሞያዎቻችንም የሙዚቃ ድግሳቸዉን ደግሰዉ ወጣቱን አስጎንጭተዉ የሚያሳክሩበትና ክብራቸዉን እንዲያጡና ከድንግልናቸዉ እንዲናወሩ የሚያደርጉበት ታላቅ ቀናቸዉ ነዉ፡፡ ጎዳናዋም ቀይ በለበሱና በአበባ ትሸማቀቃለች፤የሆቴል መኝታ ክክሎችም በደምና በበደል ይጨማለቃሉ፡፡ ወይኖች ለሐዘን ይጎነጫሉ፣ሻምፓኞች ይረጫሉ፣ገንዘቦች እንዲሁ ይመነዘራሉ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርኮች ይጨናነቃሉ፣የፌስ ቡክ ገፆች እንዲሁ በመልካም ምኞት ገላጮች ትዋከባለች፣ጓደኛ የሌላቸዉ አንገታቸዉን ደፍተዉ ክብራቸዉን ጠብቀዉ ያመሻሉ፡፡ እግዚኦ!

ማክሰኞ 12 ፌብሩዋሪ 2013

ማህበራዊ ድረ ገፆች እና ንባብ



”ማህበራዊ ድረ ገፆች እና ንባብ

ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት ኤጀንሲ ባለፈዉ የካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ከ7፡30-11፡00 የቆየ በ”ማህበራዊ ድረ ገፆች እና ንባብ” በሚል ርዕስ ዉይይት አካሂዶ ነበር: በዕለቱም የተለያዩ ምሁራን ተገኝተዉ ነበር::  ከነዚህም መካከል አወያይ የነበሩት ገጣሚና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ የጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ ነፃነት ተሰፋዬ እና ሌሎች የዉይይቱ አቅራቢዎች ታዋቂዉ የ”ዳንኤል እይታዎች” ብሎገር ዲ/ን እና ደራሲ ዳንኤል ክብረት ታዋቂዉ የ”እማማ ጨቤ” ተከታታይ ድራማ ደራሲ የሬድዮ ባለሙያ ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃ ሲሆኑ :
አቶ ነፃነት በጥናታቸዉ ለመዳሰስ የሞከሩት
ü  ማህበራዊ ድረ ገፆች እና ንባብ
ü  ማህበራዊ ድረ ገፆች ያላቸዉ አጠቃላይ አዉንታዊ አስተዋፅኦ
ü  ማህበራዊ ድረ ገፆች በንባብ ባህል ላይ የፈጠሩት አዉንታዊ እና አሉታዊ ተፅእኖ…ወዘተ


ማህበራዊ ሚድያ፡-
Ø  Internet forums
Ø  Weblogs /blogs
Ø  Social blogs
Ø  Micro blogging
ከነዚህ ማህበራዊ ሚድያዎች መካከል ፌስቡክ ቁጥር አንድ እንደመሆኑ መጠን በኣለም ላይ ከአንድ ቢልዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን አጥኝዉ አቶ ነፃነት አፍሪካ አዉሮፓ ኤስያ ና አሜሪካን በመከተል 48.3 ሚልዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ተናግረዋል፤ከዚህ ዉስጥም የተወሰነዉ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ (883160 ሰዎች ሲሆኑ 72 በመቶ ወንዶች ቀሪዉ 28 በመቶ ሴቶች ናቸዉ) ከዓለም በ86ኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፤ … በጥናቱ መሰረት፡፡
አክለዉም እነዚህ ማህበራዊ ድረ ገፆች፡
§  አማራጭ የንባብ መድረኮች
§  ሃሳብን በነፃነት የመናገርና የመፃፍ
§  በዉድ ዋጋ የሚገኙ መፃህፍትን ለማንበብ
§  አንብቦ  ሃሳብን ለመለዋወጥና ለመከራከር
§  ለተማሪዎች በቂ መፃህፍትን ለመስጠት
§  መፃህፍትን በሚፈለገዉ መጠን ለማቅረብ … ወዘተ
በነዚህ ማህበራዊ ድረ ገፆች፡
v  በአሜሪካ 43 በመቶ ነዋሪዉ ንባባቸዉን አዳብረዋል
v  በኢንግሊዝ 20 በመቶ ልብወለድ 67 በመቶ ድረ ገፅ 55 በመቶ ኢሜል 46 በመቶ ብሎጎችን ተጠቃሚ ሆነዋል
v  በአገራችንም እንዲሁ ከእለት ወደ ዕለት የንባብ ባህል እየዳበረ መሆኑን በማስረጃ አስደግፈዋል፡፡
ከህብረተሰቡ ወደ ማህበራዊ ድረ ገፅ ማዘንበል የተነሳ በአለም ታዋቂዉ News week  መፅሔት ከ2013 የፈረንጆች ዘመን መለወጫ ጥር ወር አንስቶ ወደ ድጅታልነት ተቀይሯል፡፡ ይህ የሚያሳየዉ ደግሞ የማህበራዊ ድረ ገፅ በአለም ላይ መስፋፋትን ነዉ፡፡
ከማህበራዊ ድረ ገፆች መካከል፡-
·         የዳንኤል እይታዎች
·         የኤፍሬም እሸቴ እይታዎች
·         የብስራት እይታ
·         የደረሰ ረታ እይታዎች
·         በቅርቡ ደሞ የበዉቀቱ ስዩም….ጥቂቶቹ ናቸዉ፡፡
·          
እነዚህ ድረ ገፆች ፋይዳቸዉ፡-
Ø  የንባብ ባህልን ያዳብራል
Ø  አማራጭ መፃህፍትን ይሰጣል
Ø  የሃሳብ ልዉዉጥን ያሰፋል
Ø  የተማሪዎችን የማጣቀሻ መፃህፍትን ይቀርፋል
አሉታዊ ተፅዕኖዉ፡-
ü  የመረጃ ተአማኒነት ያሳጣል
ü  የቆዩ መፃህፍትን መዘንጋት
ü  የፀሃፊዎችን ድካም ዋጋቢስ ያደርጋል
ወዘተ…
ይህንን ዝግጅት ያዘጋጀዉ ኤጀንሲዉ ጅማሮዉ ይበል የሚያሰኝ ነዉ፡ እኔም በበኩሌ የንባብ ባህላችንን እናዳብር ዘንድ ተማፅኖዬን አቀርባለሁ፡፡ኤጀንሲዉንም ሆነ አቅራቢዎችን በመቀጠልም ታዳሚዎችን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡መልካም የንባብ ዘመን!


ጦማሩን ስለጎበኙ አመሰግናለሁ!

መልካም ነገርን ለሌሎች ማጋራት ባህላችን እናድርግ፤ ላልደረሰዉ በማጋራት ድርሻችንን እንወጣ፡፡

ትቶ እና ችሎ

  ትቶ እና ችሎ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በደረሰ ረታ ብጹዕነታቸው ለሶስት አሥርት አመታት እኛ በማናውቀው እግዚአብሔር በሚያውቀው በብዙ መከራ በብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያሳለፉት። ...